ቀጥታ፡

በባሌ ዞን በተጠናቀቀው የ2015 የበጀት ዓመት 457 ኪሎ ሜትር የገጠር መንገድ ጥገና ሥራ ተከናውኗል

ሮቤ፤ ሐምሌ 22 /2015 (ኢዜአ)፡-በባሌ ዞን በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ457 ኪሎ ሜትር የገጠር መንገድ ጥገና ሥራ ማከናወኑን በኦሮሚያ መንገዶችና ሎጂስቲክ ቢሮ የባሌ ዞን የመንገድ ጥገና ጽህፈት ቤት አስታወቀ። 

የጽህፈት ቤቱ ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ንጉሴ ከበደ እንደተናገሩት፤ በዞኑ በ2015 የበጀት ዓመት ህብረተሰቡ ቅሬታ ሲያነሳበት የነበረ 457 ኪሎ ሜትር የገጠር መንገድ የጥገና ሥራ ተከናውኗል። 

ጽህፈት ቤቱ እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻ 450 ኪሎ ሜትር የሚረዝም መንገድ የጥገና ሥራዎች ለማከናወን ያቀደ ሲሆን 457 ኪሎ ሜትር በማከናወን ከዕቅድ በላይ መፈጸሙን አመልክቷል። 

ኢንጂነር ንጉሴ እንዳሉት፣ ጥገና ከተደረገላቸው መንገዶች መካከል 191  ኪሎ ሜትሩ ከባድ ጥገና  የተደረገለት ነው። 

ሮቤ-ኢሉ-ሳምብቱ፤ ጋሰራ-ቢርቢርሳ፣ ሀረና የገጠር መንገድ ጥገና ሥራ ከተከናወነላቸው መንገዶች መካከል መሆናቸው ተጠቁሟል። 

ሥራ አስኪያጁ፣ ለጥገና ሥራው ማስፈጸሚያ ከ26 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉን ተናግረዋል፡፡ 

መንግሥት ከፍተኛ ወጪ በማውጣት አዳዲስና ነባር መንገዶችን መገንባትም ሆነ ጥገና ሲያደርግ አሸከርካሪዎችና ሕብረተሰቡ  አጠቃቀም ላይ ጥንቃቄ እንዲያደርጉም መክረዋል። 

በዞኑ ወቅቱን ጠብቆ የሚደረገው ጥገና ለመንገድ ደህንነት ጉልህ ድርሻ እንዳለው የሲናና ወረዳ ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡ 

ከነዋሪዎቹ መካከል ሐጅ መሐመድ አህመድ በሰጡት አስተያየት ከዚህ በፊት በአካባቢያቸው የተሰራ የገጠር መንገድ ወቅታዊ ጥገና ስለማይደረግለት በክረምት ወቅት አገልግሎት እንደማይሰጥ አስታውሰዋል።


 

በዚህም በተደጋጋሚ ቅሬታ ሲያቀርቡ እንደነበር ገልጸው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ጥገና በመደረጉ  አገልግሎቱን እያገኙ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 

ለገጠር መንገድ የሚደረገው ጥገና መንገዱ ክረምት ከበጋ አገልግሎት እንዲሰጥ ከማድረግ በተጓዳኝ ለመንገድ ደህንነት ጉልህ ድርሻ አለው ያሉት ደግሞ ሌላው የወረዳው ነዋሪ አቶ በድሪ አማን ናቸው፡፡ 


 

በባሌ ዞን ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ በገጠር መንገድ ተደራሽነት መርሃ ግብር ከ2 ሺህ ኪሎ ሜትር የሚበልጥ የገጠር መንገድ ተሰርቶ ለህብረተሰቡ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ከዞኑ መንገዶችና ሎጂስቲክ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም