ቀጥታ፡

የዓለም ባንክ ፕሬዝዳንት አጃይ ባንጋ በሚቀጥለው ሳምንት ኢትዮጵያን ይጎበኛሉ

አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 22/2015(ኢዜአ):- የዓለም ባንክ ፕሬዝዳንት አጃይ ባንጋ ሐምሌ 24 እና 25/2015 በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደርጋሉ።

ጉብኝቱ 78 ዓመታት ያስቆጠረው ተቋም አዳዲስ አሰራሮችን ለመፍጠር የያዘውን አዲስ ግብ ለማሳካት የጀመረው ጉዞ አካል መሆኑ ተገልጿል።

በኢትዮጵያ ላሉ ወጣቶች እና ሴቶች የስራ እድሎች መፍጠር የሚቻልባቸውን ሁኔታዎች መለየት የባንጋ ጉብኝት ዋንኛ ትኩረት መሆኑ ነው የተጠቆመው።

ባንጋ በቆይታቸው የጨርቃ ጨርቅ እና የጫማ አምራች ፋብሪካዎችንና ከአርሶ አደሮች ጋር ትስስር ያላቸውን የብቅል ማምረቻዎችን የሚጎበኙ ሲሆን አነስተኛ የንግድ ስራ ባለቤቶችንም እንደሚያነጋግሩ የገንዘብ ሚኒስቴር የዓለም ባንክን ዋቢ አድርጎ ያወጣው መረጃ ያመለክታል።

በኢትዮጵያ የግሉ ዘርፍ ኢንቨስትመንት ማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከንግድ መሪዎች እና ከተለያዩ ተቋማት ዋና ስራ አስፈጻሚዎች ጋር ውይይት እንደሚያደርጉ ተመላክቷል።

ፕሬዝዳንቱ በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ ከኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ዓለም ባንክ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ግንኙነት እና ትብብር ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ እንደሚመክሩ ተገልጿል።

ከአፍሪካ ሕብረት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋርም ባንኩ እና ሕብረቱ ያላቸውን ትብብር ማጎልበት በሚቻልባቸው አማራጮች ላይ ይወያያሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ነው የተጠቀሰው።

የዓለም ባንክ የምስራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ቪክቶሪያ ክዋካ እና የዓለም አቀፉ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን የኢንዱስትሪዎች ምክትል ፕሬዝዳንት መሐመድ ጉሌድ ከአጃይ ባንጋ ጋር ወደ ኢትዮጵያ ይመጣሉ ነው የተባለው።

የዓለም ባንክ ፕሬዝዳንት የኢትዮጵያ ጉብኝታቸውን አጠናቀው ወደ ናይጄሪያ እንደሚያመሩ ተጠቁሟል።

ፕሬዝዳንቱ ከዚህ ቀደም ፔሩ፣ ጃማይካ እና ሕንድን መጎብኘታቸው ይታወቃል።

ትውልደ ሕንዳዊው የአሜሪካ ዜጋ አጃይ ባንጋ በሚያዚያ/2015 የዓለም ባንክ 14ኛ ፕሬዝዳንት ሆነው መመረጣቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም