ቀጥታ፡

የዓለም አቀፍ የዕቃ አስተላላፊዎች ማኅበራት ፌደሬሽን (ፊያታ) ጉባኤ ነገ በአዲስ አበባ ይካሄዳል

 አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 21/2015 (ኢዜአ)፡- የዓለም ዕቃ አስተላላፊዎች ማኅበራት ፌደሬሽን (ፊያታ) ጉባኤ በነገው ዕለት በአዲስ አበባ ይካሄዳል።

የፌዴሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር ጀነራል ዶክተር ስቴፈን ግራበር ለሁለት ቀናት የሚካሄደውን ጉባኤ አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፤ የተለያዩ የዓለም አገራት የሎጂስትክስ ማህበራት ሊቀ መናብርትን ጨምሮ 2 ሺህ 500 እንግዶች በጉባኤው ይሳተፋሉ ብለዋል።

ኢትዮጵያ በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት በሎጂስትክስ ዘርፉ አመርቂ ውጤት ማስመዝገቧን ዳይሬክተር ጀነራሉ ገልጸዋል።

በነገው እለት የሚጀመረው ጉባኤም በኢትዮጵያ አጠቃላይ የሎጂስቲክስ ዘርፉን አሰራር ወጥ ለማድረግ የመፍትሔ ሀሳብ እንደሚቀርብበት አስረድተዋል፡፡  

 የኢትዮጵያ ዕቃ አስተላላፊዎች የጭነት አገልግሎት ማህበር የቦርድ ምክትል ፕሬዘዳንት አቶ ዳዊት ውብሸት በበኩላቸው፤ በጉባኤው ከሚነሱ ጉዳዮች መካከል የአየር ጭነት ገበያን ለደንበኞት ተስማሚ የማድረግ ጉዳይ አንዱ ነው ብለዋል።


 

ጉባኤው ኢትዮጵያ በአካባቢው አገራት በአየር ጭነት ትራንስፖርት ያላትን ስትራቴጂካዊ ሚና ለማስገንዝብ መልካም እድል የሚፈጥር ይሆናል ነው ያሉት።

የአፍሪካ አገራት በዘርፉ ያላቸውን ፍላጎት ለማወቅና አገራቱ በተገቢው ሁኔታ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን አሰራር ለማመቻቸትም እንደሚረዳም አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ በ2026 የዓለም የዕቃ አስተላላፊዎች ማኅበራት ፌዴሬሽን የ100ኛ አመት በዓልን ለማዘጋጀት ያቀረበችውን ጥያቄ ተቀባይነት እንዲያገኝ ከማድረግ አንፃርም የጉባኤው መካሄድ ሰፊ እገዛ እንደሚያደርግም አንስተዋል። 

በመግለጫው ወቅት በዓለም ዕቃ አስተላላፊዎች ማኅበራት በኩል ስልጠና ለወሰዱ 28 ኢትዮጵያውያን በፌዴሬሽኑ በኩል የምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም