ቀጥታ፡

መንግስት በ2016 የተሻለ ገቢ መሰብሰብ የሚያስችለውን የህግ ማዕቀፍና የአሰራር ማሻሻያ እያደረገ ነው - የገቢዎች ሚኒስትር አይናለም ንጉሴ

አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 21/2015 (ኢዜአ)፡-  መንግስት በ2016 በጀት ዓመት የተሻለ ገቢ መሰብሰብ የሚያስችለውን የህግ ማዕቀፍና የአሰራር ማሻሻያ እያደረገ መሆኑን የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ አይናለም ንጉሴ ገለጹ፡፡

ሚኒስቴሩ በተጠናቀቀው የ2015 በጀት ዓመት አፈፃፀምና በቀጣይ እቅድ ዙሪያ ከከፍተኛ ግብር ከፋዮች ጋር ውይይት አድርጓል።


 

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ግብር ከፋዮች የሀገሪቱን የውስጥ ገቢ 71 በመቶ እንዲሁም ሚኒስቴሩ የሚሰበስበውን 43 በመቶ የሚሸፍኑ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሾች ናቸው፡፡

የከፍተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት መረጃ እንደሚያሳየው በ2015 በጀት ዓመት ከከፍተኛ ግብር ከፋዮች 176 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ የተሰበሰበ ሲሆን በተያዘው በጀት ዓመት 226 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ዕቅድ ተይዟል፡፡

የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ አይናለም ንጉሴ በውይይቱ ላይ እንዳሉት፤ እንደ ሀገር በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከተለያዩ የገቢ አርዕስቶች 450 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 442 ቢሊዮን ብር ማሳካት ተችሏል፡፡

በዚህ መነሻነት በተያዘው በጀት ዓመትም 529 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ የተለያዩ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በዘንድሮው በጀት ዓመት ለመሰብሰብ የታቀደውን ግብ ለማሳካት ሥራን በመከፋፈል የአገልግሎት አሰጣጡን ማዘመንና ውጤታማ ማድረግ ላይ መስራት የሁሉም ትኩረት መሆን አለበት ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በተለያዩ ዘርፎች ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገበ መምጣቱ በበጀት ዓመቱ የሚሰበሰበውን የገቢ መጠን ከፍ አድርጎታል ያሉት ሚኒስትሯ፤ የግብር ከፋዮች ታማኝነት ገቢውን ለማሳደግ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከአገራዊ የመልማት ፍላጎትና እድሎች አንፃር የሚሰበሰበው ገቢ አሁንም በቂ እንዳልሆነ ጠቅሰው፤ በበጀት ዓመቱ ውጤታማ ገቢ መሰብሰብ የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል።

ከዚህ ባለፈ የመንግስትን ገቢ የሚሰውሩ አካላት ተጠያቂ የሚሆኑበት ጠንካራ አሰራር መዘርጋቱን ነው ያነሱት።

የኢትዮጵያ የታክስ አስተዳደር አዋጅ በፍላጎት ላይ የተመሰረተ ታክስ ማሳወቅን ቢደነግግም፤ አዋጁ ግብር ከፋዮች ያሳወቁት ወጭና ገቢ በትክክል መሰራቱን የሚያረጋግጥበት አሰራርን ማካተቱን ጠቁመዋል፡፡

የሚጠበቅባቸውን የመንግስት ገቢ በአግባቡ መክፈል የማይፈልጉ ግብር ከፋዮች በተጭበረበረ ደረሰኝ የግብይት ሂሳብ እንደሚያወራርዱ በምርምራ የደረስንባቸው አሉ ብለዋል፡፡

በመሆኑም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የገቢና ወጭ ደረሰኞችን ዲጂታላይዝ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩን ነው የጠቆሙት፡፡

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም