የ12ኛ ክፍል የማህበራዊ ሳይንስ ፈተና በሰላም ተጠናቋል - ትምህርት ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የ12ኛ ክፍል የማህበራዊ ሳይንስ ፈተና በሰላም ተጠናቋል - ትምህርት ሚኒስቴር
ሀዋሳ ፤ ሐምሌ 21/2015(ኢዜአ)፦ በዩኒቨርሲቲዎች ሲሰጥ የነበረው የ12ኛ ክፍል የማህበራዊ ሳይንስ አገር አቀፍ ፈተና በሰላም መጠናቀቁን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
የትምህርት ሚንስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እንደገለጹት የዘንድሮው የማህበራዊ ሳይንስ ዘርፍ የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ አገር አቀፍ ፈተና ያለ ምንም እንከን በሰላም ተጠናቋል።
የፈተናው ሂደትን በተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር እንደጎበኙ የተናገሩት ፕሮፌሰሩ “የፈተናው ሂደት በሰላማዊና በታቀደው መሰረት ተጠናቋል” ብለዋል።
ከአምስት መቶ ሺህ በላይ ተፈታኞች የሚገኙበትና በቁጥር ብዙ ተማሪዎች የተስተናገዱበት እንደነበር ገልጸው ፤ ካለፈው ዓመት በሁሉም መንገድ የተሻለ እንደነበር ተናግረዋል።
“ካነጋገርናቸው ተማሪዎች እንደተረዳነው ፈተናው በጣም ጥሩ እንደነበርና ካለፈው ዓመት አንጻር ሲታይ የተሻለ ውጤት ይመዘገብበታል ብዬ እጠብቃለሁ” ነው ያሉት ፕሮፌሰር ብርሀኑ።
የተፈጥሮ ሳይንስ ተፈታኞች ከነገ ጀምሮ ወደ ሚፈተኑባቸው ዩኒቨርሲቲዎች እንደሚገቡ የተናገሩት ፕሮፌሰር ብርሀኑ በመጪው ሳምንት ፈተናው እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።
በትምህርት ሚንስትሩ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ የተመራ ቡድን ዛሬ ከሰዓት በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሳውላ ካምፓስ እየተሰጠ ያለውን የ12ኛ ክፍል ማህበራዊ ሳይንስ ፈተና ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።