በኢትዮጵያና በሩሲያ መካከል ያለውን የመረጃ፣ የቢዝነስና የመሰረተ ልማት ትብብር የሚያጠናክሩ ስምምነቶች ተፈረሙ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያና በሩሲያ መካከል ያለውን የመረጃ፣ የቢዝነስና የመሰረተ ልማት ትብብር የሚያጠናክሩ ስምምነቶች ተፈረሙ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 21/2015(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያና በሩሲያ መካከል ያለውን የመረጃ፣ የቢዝነስና የመሰረተ ልማት ትብብር የሚያጠናክሩ ስምምነቶች ተፈርመዋል።
ስምምነቶቹ በሩሲያ አፍሪካ ጉባኤ ላይ እየተሳተፈ በሚገኘው የኢትዮጵያ የልዑካን ቡድን አባላት የተፈረሙ ናቸው።
በኢትዮጵያና በሩሲያ መካከል አለም አቀፍ የመረጃ ደህንነትን በተመለከተ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት የፈረሙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታው አምባሳደር ምስጋኑ አርጋና የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ናቸው።
ስምምነቱ በአለም አቀፍ ደረጃ የመረጃ ደህንነት ዘርፍ ላይ አቅምን ለመገንባት፤ የሳይበር ደህንነትን ማስጠበቅ እንዲሁም የመሰረተ ልማትና የቴክኖሎጂ አቅምን በጋራ ለመጠቀም የሚያስችል መሆኑም ተገልጿል።
የሁለቱን ሃገራት የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ዘርፍ ማሳደግ ያለመው ስምምነትም ከተፈረሙት ስምምነቶች አንዱ ነው።
ስምምነቱን የፈረሙት የሩሲያ የትራንስፖርት ሚኒስትር ኢጎር ቻሊክ ሩሲያ ከአፍሪካ ሃገራት ጋር ያላትን ትስስር ለማጠናከር የኢትዮጵያ አየርመንገድ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ እና በሩሲያ የጉምሩክ አገልግሎት ሃላፊ ሩስላን ዳቪዶፍ መካከል የተፈረመው ስምምነትም በሁለቱ ሃገራት መካከል በዘርፉ ያለውን የክፍያና አገልግሎት ስርአት ለማዘመን የሚያስችል እንደሚሆን ተነግሯል።
በተጨማሪም ስምምነቱ የኢትዮጵያና የሩሲያን የንግድ ግንኙነት ለማጠናከር የሚያሰችል እንደሆነም ተገልጿል።