ስራ ከመፈለግ ይልቅ ስራ መፍጠር በመቻላችን ከራሳችን አልፈን ለሌሎችም ስራ መፍጠር ችለናል -- የከፍተኛ ትምህርት ተመራቂዎች - ኢዜአ አማርኛ
ስራ ከመፈለግ ይልቅ ስራ መፍጠር በመቻላችን ከራሳችን አልፈን ለሌሎችም ስራ መፍጠር ችለናል -- የከፍተኛ ትምህርት ተመራቂዎች
መቱ ፤ ሐምሌ 21/2015 (ኢዜአ)፡- ስራ ከመፈለግ ይልቅ ስራ መፍጠር በመቻላችን ከራሳችን አልፈን ለሌሎች ስራ መፍጠር ችለናል ሲሉ ከከፍተኛ ትምህርት የተመረቁ የመቱ ከተማ ወጣቶች ገለጹ።
ከተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተመርቀው የመንግስት ስራን ብቻ ሳይጠብቁ በአካባቢያቸው መስራት የሚችሉትን ለይተው በትንሽ ካፒታል ወደ ስራ የገቡት የመቱ ከተማ አስተዳደር ወጣቶች ራሳቸውን ከመቻል አልፈው ለሌሎችም የስራ ዕድል መፍጠር መቻላቸውን ተናግረዋል።
የካሚል አወልና ጓደኞቻቸው ሕብረት ማኅበር መስራቾች የሆኑት ካሚል አደምና አወል ናስር ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በዲግሪ የተመረቁ ናቸው።
ወጣት ከማል አወል፣ ከሶስት ዓመት በፊት ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተመረቁት ወጣቶቹ ስራ ከመፈለግ ይልቅ ስራ ለመፍጠር አቅደው ወደ ስራ መግባታቸውን አስታውሷል።
ወጣቶቹ የዛሬ ሶስት ዓመት በማኅበር ተደራጅተው ከ70 ሺህ ብር በማይበልጥ መነሻ ካፒታል ወደ ንግድ ስራ መሰማራታቸውን ይናገራሉ።
''አካባቢያችንን በመቃኘት መስራት የምንችለውን ነገር ከለየን በኋላ በብድር ባገኘነው ጥቂት መነሻ ካፒታል የንግድ ስራ ጀመርን'' ብሏል።
በጀመሩት የንግድ ስራ ራሳቸውን ከመቻል አልፈው ለሌሎችም የስራ ፈላጊዎች የስራ ዕድሎችን መፍጠር እንደቻሉ ይናገራል።
በአሁኑ ሰዓትም 4 ሚሊዮን ብር የሚደርስ ካፒታል የማንቀሳቀስ ደረጃ ላይ የደረሱ መሆናቸውንም ነው የገለጸው።
በንግድ ስራ የተሰማሩት ወጣቶች ለሰባት ያህል ሰዎች የስራ ዕድል መፍጠር እንደቻሉም ጨምረው ተናግረዋል።
በተመሳሳይ ሁኔታ በከተማዋ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመርቀው በተማሩት ሙያ የራሳቸውን ስራ በመፍጠር ወደ ስራ የገቡት የ'ዊዝደም ብሎኬት ማምረቻ' ማኅበር አባላት በስራቸው ውጤታማ እየሆኑ ስለመሆናቸው ይናገራሉ።
በ2005 ዓ.ም. ከጅማ ዩኒቨርሲቲ በማርኬቲንግ ትምህርት መመረቁን የሚገልፀው የማኅበሩ አባል ኑርሁሴን ከድር በ2009 ዓ.ም. ስራውን ሲጀምሩ ዕውቀት፣ የስራ ሐሳብና ዓላማ ብቻ እንደነበራቸው ይገልፃል።
ከብድርና ቁጠባ ማኅበራት ባገኙት ትንሽ መነሻ ካፒታል ስራውን የጀመሩ መሆኑን በማንሳትም ጠንክረው በመስራት ዛሬ ላይ ትላልቅ ማሽኖችን በመጠቀም ስራቸውን ማስኬድ እንደቻሉ ገልጿል።
ፉአድ መሐመድኑር በበኩሉ ራስንም ሆነ ሀገርን ለመለወጥ የራስን ስራ ፈጥሮ መንቀሳቀስና ኢንተርፕሪነር በመሆን ከጠባቂነትና ከጥገኝነት መላቀቅ የግድ ነው በማለት ይናገራል።
ማኅበራቱ በአሁኑ ሰዓት ከ70 በላይ የሚሆኑ የከተማዋ ነዋሪዎችን የስራ ዕድል ተጠቃሚዎች ማድረግ እንደቻሉ ነው የገለፁት።
የስራ እድል የተፈጠረላቸው ዜጎች በሰራተኝነት ከሚያገኙት ክፍያ ባሻገር እያገኙ ባሉት ሙያና ልምድ የራሳቸውን ድርጅት ለመክፈት እንደሚያቅዱም ገልፀዋል።
በመቱ ከተማ አስተዳደር በተለይ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተመረቁ ወጣቶች የራሳቸውን ስራ ፈጥረው መስራት እንዲችሉ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን የከተማው የስራ ዕድል ፈጠራና ሙያ ጽሕፈት ቤት ገልጿል።
የጽህፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ ታጁዲን ጥሩነህ፣ ስራ ፈላጊዎችን በማህበር በማደራጀት ብድርን ጨምሮ ሌሎች አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ከሌሎች አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመትም ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተመረቁ ወጣቶችን ጨምሮ ከ4 ሺህ በላይ ወጣቶችን በማኅበር በማደራጀት በተለያዩ ስራዎች ላይ እንዲሰማሩ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።
ለመስሪያ ቦታ የሚሆኑ ሼዶችን ወጣቶቹ ቅድሚያ ተሰጥቷቸው እንዲያገኙ ማድረግን ጨምሮ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ብድርም የተመቻቸላቸው መሆኑንም አክለው ገልፀዋል።