መንግስት በኢትዮጵያ በአውቶሞቲቭ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ላይ ለመሰማራት ለሚፈልጉ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል- የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት በኢትዮጵያ በአውቶሞቲቭ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ላይ ለመሰማራት ለሚፈልጉ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል- የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን
አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 21/2015 (ኢዜአ)፦ መንግስት በኢትዮጵያ በአውቶሞቲቭ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ላይ ለመሰማራት ለሚፈልጉ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ።
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ኢንጂነር ለሊሴ ነሜ ከጀርመኑ የቮልስዋገን የመኪና አምራች ኩባንያ የአፍሪካ ከፍተኛ ኃላፊዎች እና በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ስቴፋን አወር ጋር ተወያይተዋል።
ውይይቱ በኢትዮጵያ በአውቶሞቲቭ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ላይ እየተደረጉ ስለሚገኙ ማሻሻያዎች ትኩረት ያደረገ መሆኑ ተገልጿል።
መንግስት በአውቶሞቲቭ ኢንቨስትመንት ዘርፍ ኢትዮጵያ ግንባር ቀደም ተመራጭ መዳረሻ እንድትሆን ፍላጎት እንዳለው እንደ ቮልስዋገን ላሉ ዓለም አቀፍ አምራቾች በዘርፉ እንዲሳተፉ እና እንዲያለሙ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልጸዋል።
የጀርመኑ ግዙፍ የመኪና አምራች ኩባንያ ቮልስዋገን እ.አ.አ በ2019 በኢትዮጵያ የመኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካ ለመክፈት የሚያስችለው ስምምነት ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር መፈራረሙ የሚታወስ ነው።
ኩባንያው ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ በመኪና ማምረት ዘርፍ የመሰማራት ፍላጎት እንዳለው ሲገልጽ ቆይቷል።