የሀረሪ ባህል፣ ታሪክ፣ ቅርስ እና ቋንቋን በማጎልበት በኩል ውጤታማ ስራዎች ተከናውነዋል-የሀረሪ ጉባዔ - ኢዜአ አማርኛ
የሀረሪ ባህል፣ ታሪክ፣ ቅርስ እና ቋንቋን በማጎልበት በኩል ውጤታማ ስራዎች ተከናውነዋል-የሀረሪ ጉባዔ
ሐረር ፤ ሐምሌ 20/2015 (ኢዜአ) ፡- የሐረሪ ጉባዔ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የሀረሪ ባህል፣ ታሪክ፣ ቅርስ እና ቋንቋን በመጠበቅና በማጎልበት በኩል ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን አስታወቀ።
የሐረሪ ጉባዔ ስድስተኛ ዙር ሁለተኛ ዓመት ሁለተኛ መበደኛ ጉባኤ የተለያዩ ሪፖርቶችን በማጽደቅ ተጠናቋል።
የክልሉ ትምህርት ቢሮ እና የክልሉ ባህል፣ ቱሪዝምና ቅርስ ቢሮ ኃላፊዎች በሀረሪ ታሪክ፣ ባህልና ቅርስ ጥበቃ እና የሐረሪን ቋንቋ ከማሳደግ አንጻር በበጀት ዓመቱ የተከናወኑ ስራዎች ሪፖርቶችን ለጉባዔው አቅርበዋል።
የክልሉ ባህል ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ተወለደ አብዶሽ እንዳሉት በጀጎል አጥር ቅርስ ጥበቃ፣ በታሪካዊ አድባራትና በሙዚየሞች ዕድሳትና የባህል ቤቶች ግንባታን አጠናቆ ለአገልግሎት የማብቃት ስራ ተከናውኗል።
እንዲሁም የሀረሪ ባህላዊ ዕደ-ጥበብ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ማህበራትን መደገፍን ጨምሮ ሌሎች የተከናወኑ ስራዎችን በሪፖርታቸው አቅርበዋል።
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙክታር ሳሊህ በክልሉ በአንደኛና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሀረሪ ቋንቋ ትምህርት አሰጣጥን የማጠናከር ተግባራት መከናወናቸውን አመልክተዋል።
በሀረሪ ቋንቋ በዲግሪ መርሃ-ግብር የሰለጠኑ ተማሪዎች ዘንድሮ ለምረቃ ማብቃት መቻሉን ኃላፊው ለአብነት አንስተዋል።
አያይዘውም በሀረሪ ቋንቋ የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርት መስጠት መጀመሩን ጠቅሰው፤ በቋንቋው የሚሰሩና የሚያስተምሩ ባለሙያዎችን አቅም የማሳደግ ስራዎች መከናወናቸውን በሪፖርቱ ጠቅሰዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በባህልና ቅርስ ጥበቃና በሀረሪ ቋንቋ ትምህርት የተከናወኑ ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አመልክተዋል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በበኩላቸው በበጀት ዓመቱ የሀረሪ ባህል፣ ታሪክ፣ ቅርስና ቋንቋን በመጠበቅና በማጎልበት በኩል ውጤታማ ስራዎች ተከናውነዋል።
በተለይ የሀረሪ አለላ ስፌት (ጌይ ሞኦት) ዓለም አቀፍ ዕውቅና አግኝቶ መለያ (ብራንድ) መሆን መቻሉና ሀረር የዓለም የቅርስ ከተሞች አባል በመሆኗ የክልሉን መልካም ገፅታ ይገነባል ብለዋል።
እንዲሁም በሀረሪ ቋንቋ ትምህርት በዲግሪ መርሃ-ግብር ሰልጣኞች ለመጀመሪያ ጊዜ ማስመረቅ መቻሉንና በሀረር የሚገኙ አራት ሙዚየሞች በሀገር አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
በተጨማሪም የጀጎል አጥር ዙሪያ አረንጓዴ ስፍራን በማልማት የቅርሱን ደህንነት ለመጠበቅ የሚከናወኑ ስራዎች የማጠናከር ስራ እንደተከናወነም አመልክተዋል።
ዘንድሮ ዕውቅና የተሰጣቸው በሀረር የሚገኙ ሙዚየሞች የቱሪዝም መዳረሻነት አቅምን ማበልፀግና መጠቀም እንደሚገባ እንዲሁም የሌሎች ሙዚየሞችን ደረጃ ለማሻሻል መስራት ይገባልም ብለዋል።
በባህልና ቅርስ ጥበቃ ዘርፍ የተካሄዱ ጠንካራ ስራዎችን ማስቀጠልና በሀረሪ ቋንቋ ትምህርት ዘርፍ ያሉ ስራዎችን ማጠናከር እንደሚገባ የጉባኤው አባላት ጠቁመዋል።
በጉባዔው የባህል ቅርስና ቱሪዝም እና የሀረሪ ቋንቋ ትምህርት ዘርፍ የ2016 ዓ.ም ዕቅድ ለጉባኤው ቀርቧል፤ ሪፖርቱና እቅዱ ላይ ሰፊ ውይይት በማካሄድ የጉባኤው አባላት በሙሉ ድምፅ አፅድቀዋል።