ቀጥታ፡

ሩሲያ የአፍሪካን ሁሉን አቀፍ ልማት ለመደገፍ ከምንጊዜውም በላይ ቁርጠኛ ናት_ ቭላድሚር ፑቲን

አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 20/2015(ኢዜአ)፦ሩሲያ የአፍሪካን ሁሉን አቀፍ ልማት ለመደገፍና ከሀገራቱ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ትብብር ከምንጊዜውም በላይ ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ገለጹ።

2ኛው የሩስያ አፍሪካ የኢኮኖሚና ሰብዓዊነት ጉባኤ በሩሲያ ቅዱስ ፒተርስበርግ ከተማ ንግድና ኤግዚቪሽን ማዕከል እየተካሄደ ነው። 
 
በጉባኤው የሩሲያ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች ተገኝተዋል።

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጉባኤውን ሲከፍቱ እንደተናገሩት የሩሲያና አፍሪካ የንግድ ግንኙነት እያደገ መጥቷል።

ሩሲያ ለአፍሪካ የምታደርገውን የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት ማሳደግ የሁልጊዜ ትኩረቷ መሆኑን ገልፀው፤ እስከ አሁን ያቀረበችውን የስንዴ ድጋፍ ታጠናክራለች ብለዋል።

ባለፉት 6 ወራት ብቻ 10 ሚሊዮን ቶን ስንዴ ለአፍሪካ ማቅረቧን ለአብነት አንስተዋል።

ከዚሀም ባሻገር የአፈር ማዳበሪያን ለዓለም ገበያ ለማቅረብ ቁርጠኝነት እንዳላት ነው ፕሬዝዳንቱ የተናገሩት።

በቀጣይም በተመረጡ የአፍሪካ ሀገራት ግማሽ ሚሊየን ቶን ስንዴ በነፃ ትራንስፖርት ለማቅረብ ቃል ገብተዋል።

አፍሪካ በምግብ ራሷን ለመቻል ለምታደርገው ጥረት በተለይ በግብርና ማዘመኛ ቴክኖሎጂ አቅርቦትና በኃይል መሰረተ ልማት ግንባታ ሩሲያ ድጋፍ ታደርጋለች ብለዋል።

ኒውክለርን ለሰላም መጠቀምን ጨምሮ የሁለትዮሽ ተጠቃሚነትን በሚያሳድጉ የጋራ የኃይል ልማት ፕሮጀክቶች ላይ በትኩረት እንደሚሰሩም ገልፀዋል።

ሩሲያ የኢንዱስትሪ ምርቶችን ወደ አፍሪካ የማቅረብ፣ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስና በዲጂታላይዜሽን እንዲሁም በሌሎች ቴክኖሎጂ ዘርፎች ያላትን ተሞክሮ ታጋራለች ብለዋል። 

ይህን ዕውን ለማድረግም የጋራ መገበያያ ገንዘብን በተመለከተ አዲስ አሰራር እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል። 

ሩሲያ ከግሎባል ሳውዝ (ከደቡብ ንፍቀ ክበብ ክፍለ ዓለም) ያላትን ትብብር ማጠናከርና አዲስ የንግድ ኮሪደር መገንባት የትኩረት አቅጣጫዋ ነው ብለዋል። 

የአፍሪካ ባቡር ግንባታን ጨምሮ ሀገራትን እርስ በርስ በማስተሳሰር፣ በንግድና ኢንዱስትሪ እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች ከሀገራት ጋር በስትራቴጂክ አጋርነት እንደምትሰራም አረጋግጠዋል። 

የአፍሪካን የሰው ኃይል ልማት ለማገዝ የነበራትንና እየሰጠች ያለውን የነፃ ትምህርት ዕድል እንደምታጠናክርም ነው ፕሬዝዳንቱ የተናገሩት።

ሀገራቸው በትምህርት ዘርፍ የጋራ ፕሮጀክቶችን በማከወንና ትምህርት ቤቶችን በመገንባት ላይ በስፋት እንደምትሰራ ገልጸዋል።  

በሁሉም አፍሪካ አገራት የሩሲያን ቋንቋ ለመስጠት እንደሚሰራ ገልፀው አስካሁን፣ በ28 ሀገራት የሩስያ ቋንቋ ትምህርት እንደተጀመረ ጠቁመዋል።

የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበርና የኮሞሮስ ፕሬዝዳንት አዛሊ አሱማኒ፤ በበኩላቸው በ21ኛው ክፍለ ዘመን የብዝሀ ድምፅ የሚሰማባት፣ በሁሉም ወገን አሸናፊነት የምትመራ ዓለምን መገንባት እንደሚገባ ገልጸዋል። 

አፍሪካ በሰውና በተፈጥሮ ሀብት ዕምቅ አቅም ቢኖራትም በሚፈለገው ልክ በትብብር ባለመስራቷ መልከ ብዙ ችግሮችን እያስተናገደች መቀጠሏን አንስተዋል። 

ሩስያ የአፍሪካ ሁነኛ አጋር ናት ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ በወሳኝ መስኮች ያለውን ትብብር እናጠናክራለን ብለዋል። 

ለአፍሪካ ነፃ ገበያ እና የ2063 አጀንዳዎች ስኬት የአፍሪካና የውጭ ሀገራት ኩባንያዎች ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑንም ተናግረዋል። 

ብዝሀ ኢኮኖሚን እውን ለማድረግ ከሩስያ ጋር መተባበር ወሳኝ በመሆኑ በግብርና፣ በጤና፣ በትምህርትና በሌሎች ዘርፎች ትብብር እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማምጣት የጋራ ልማት ይሻል ብለዋል።

የሩሲያ-አፍሪካ ትብብር በአፍሪካ የተጀመረውን የኢንዱስትሪ አብዮት የበለጠ ለማጠናከር ትልቅ መሰረት የሚጥል መሆኑን ጠቅሰው በግሬይን ዲል (የስንዴ ስምምነት) ሩስያ ያቀረበችው ስንዴ ለአፍሪካ ትልቅ ትርጉም እንደነበረው አንስተዋል።

በአፍሪካ ሰላምና ፀጥታ ለማስፈን መተባበርና በጋራ መስራት እንደሚጠይቅ ገልፀው፤ የሁለትዮሽ ተጠቃሚነትና መከባበር ላይ ያተኮረው የሩስያ አፍሪካ ትብብር መጠናከር እንዳለበት አንስተዋል።  

የሩሲያና ዩክሬይን ጦርነት በሰላም እንዲፈታ አፍሪካ የሰላም ተልዕኮ ሚናዋን መወጣቷን ትቀጥላለች ብለዋል። 
 በሌላ በኩል አፍሪካ የቡድን 20 አባል እንድትሆንም ጠይቀዋል።

ለሁለት ቀናት የሚቆየው ጉባዔው የአፍሪካና የሩስያን ሁለንተናዊ ግንኙነት ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሚያስችሉ ስምምነቶች እንደሚደረጉበት ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም