በኢትዮጵያና በሩሲያ መካከል ለረጅም ዓመታት የዘለቀውን የታሪክ፣ የባህልና የዲፕሎማሲ ትስስር የሚያንፀባርቅ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ግንኙነት ሊኖራቸው ይገባል- ሰላማዊት ካሳ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያና በሩሲያ መካከል ለረጅም ዓመታት የዘለቀውን የታሪክ፣ የባህልና የዲፕሎማሲ ትስስር የሚያንፀባርቅ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ግንኙነት ሊኖራቸው ይገባል- ሰላማዊት ካሳ
አዲስ አበባ ሐምሌ 20/2015(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያና በሩሲያ መካከል ለረጅም ዓመታት የዘለቀውን የታሪክ፣ የባህልና የዲፕሎማሲ ትስስር በአግባቡ የሚያንፀባርቅ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ግንኙነት ሊኖራቸው እንደሚገባ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ ተናገሩ።
በሩሲያዋ ቅዱስ ፒተርስበርግ ከተማ በሚካሄደው የአፍሪካ ሩሲያ ጉባኤ ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት ሚኒስትር ዴኤታዋ ከሩሲያ የዲጂታል ልማት፣ ኮሙኒኬሽንና ማስ ሚዲያ ምክትል ሚኒስትር ቤላ ቼርኬሶቫ ጋር ተወያይተዋል።
በውይይታቸውም አፍሪካውያን የዓለም አቀፍ የሚዲያ አማራጮቻቸውን ለማስፋት እንዲችሉ በሩሲያ የሚገኙት ትልልቅ መገናኛ ብዙሃን የአቅም ግንባታ ስራዎችን መስራት እንደሚገባቸው አንስተዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ሃሰተኛ መረጃዎች፣ የጥላቻ ንግግር እና ተመሳሳይ ችግሮች እያመጡ ያሉትን ጉዳት ለመቀነስ ሁለቱ ሃገራት ልምድ ለመለዋወጥና ውጤታማ የሆኑ አሰራሮችንም ለመተግበር ተስማምተዋል።
የመንግስት አጀንዳዎችን ለሁሉም ዜጎች ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችሉ የአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች አጠቃቀም ወሳኝ መሆኑን በማንሳት ለኢትዮጵያ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ስልጠናና የትምህርት እድሎችን ሩሲያ ለመስጠት ፍላጎት እንዳላት ምክትል ሚኒስትሯ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በከፍተኛ ደረጃ በቱሪዝም ዘርፍ ላይ እየሰራች ነው ያሉት የመንግስት ኮሙኒኬሽን ሚኒስትር ዲኤታዋ ሰላማዊት ካሳ ይህንንና ሌሎች የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለማስተዋወቅ ሚዲያው ትልቅ ሚና አለው ብለዋል።
የሁለቱ ሃገራት የሚዲያ ሥራም የሃገራቱን ግንኙነት ወደሚመጥን ደረጃ ከፍ ማድረግ እንደሚገባ እንዲሁም ኢትዮጵያ የአፍሪካ የዲፕሎማሲ መናኽሪያ በመሆንዋ የሩሲያ ሚዲያዎች በአዲስ አበባ የኢትዮጵያ ሚዲያዎችም በሩሲያ ቢሮ እንዲከፍቱ ለማገዝ ተስማምተዋል።