ቀጥታ፡

የኢትዮጵያና የደቡብ አፍሪካ የባለሙያዎች ውይይት በአዲስ አበባ መካሄድ ጀመረ

አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 20/2015(ኢዜአ)፦ስድስተኛው የኢትዮጵያና የደቡብ አፍሪካ የጋራ የሚኒስትሮች የከፍተኛ ባለሙያዎች ውይይት ዛሬ በአዲስ አበባ መካሄድ ተጀምሯል።

በጋራ መድረኩ መክፈቻ ላይ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ፍሰሃ ሻወል ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል።

አምባሳደር ፍሰሃ በመክፈቻ ንግግራቸው የኢትዮጵያ እና የደቡብ አፍሪካ የሁለትዮሽ ዲፕሎማሲያዊ ጠንካራ እና ረጅም እድሜ ያስቆጠረ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህ የቆየ ወዳጅነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የኢትዮጵያ ፍላጎት እንደሆነ ጠቁመው የባለሙያዎቹ የጋራ የምክክር መድረክ ትብብሩ የሚጠናከርበትን ሁኔታ ለማመላከት እንደሚረዳ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር እየሰራች መሆኑና በሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ ባለሙያዎች መካከል የሚደረገው ውይይት የነበሩትን የሁለትዮሽ ግንኙነቶች የበለጠ ለማጠናከር እና አዳዲስ የትብብር ዘርፎችን መለየት ላይ ትኩረት እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።

የደቡብ አፍሪካ የዓለም ዓቀፍ ግንኙነትና ትብብር መምሪያ የአፍሪካ ጉዳዮች ተጠባባቂ ጀነራል ዳይሬክተር ሴላኔ ሞኩኤና በበኩላቸው የሁለቱ ሀገራት ትብብርና ወዳጅነት ከአፓርታይድ ትግል ዘመን ጀምሮ እንደሆነ አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ኔልሰን ማንዴላን ጨምሮ የደቡብ አፍሪካ ነጻነት ታጋዮች የሚስተናገዱባት ቤታቸው እንደነበረች ጠቅሰዋል።

በፕሪቶሪያ የተደረሰውን የሰላም ስምምነት አፈጻጸም ማድነቃቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም