ቀጥታ፡

ኢትዮጵያና ፓኪስታን በአቬዬሽን ዘርፍ ያላቸውን ግንኙነት በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ዙርያ ምክክር አካሄዱ

አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 20/2015 (ኢዜአ) ፦ ኢትዮጵያና ፓኪስታን በአቬዬሽን ዘርፍ ያላቸውን ግንኙነት በሚያጠናክሩባቸው ጉዳዮች ዙርያ ምክክር አካሄዱ።

በፓኪስታን የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሰደር ጀማል በከር ከፓኪስታን የአቬዬሽንና የባቡር መሰረተ-ልማት ሚኒስትር ካዋጃ ሰአድ ረፊቅ ጋር ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም ኢትዮጵያና ፓኪስታን በአቬዬሽን ዘርፍ ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር እንዲሁም በዘርፉ አሁን ያለውን ግንኙነት በተሻለ ማሳደግ የሚያስችሉ ጉዳዮችን አንስተዋል።

በዘርፉ የሚካሄደው የጠነከረ ግንኙነት በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የህዝብ ለህዝብ እና የንግድ ግንኙነት የበለጠ ማሳደግ እንደሚያስችልም ተገልጿል።

በውይይቱ የአቬዬሽን ዘርፉ ትስስር ማደግ ለንግድ፣ ለቱሪዝም እና ለኢንቨስትመንት ዘርፍ ማደግ የሚያስገኘው ጥቅም የላቀ መሆኑም ተነስቷል።

የሁለቱ አገራት መንግስታት ይህንን ለማጠናከር እንደሚሰሩ አጽንኦት መስጠታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም