ቀጥታ፡

አፍሪካዊ ማንነትን የተላበሰ የዲጂታል ኢኮኖሚ በመገንባት እና የቴክኖሎጂ ባለቤትነትን በማረጋገጥ የአፍሪካን ብልጽግና ማረጋገጥ ይቻላል--አቶ ሰለሞን ሶካ

አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 20/2015 (ኢዜአ) ፦ አፍሪካዊ ማንነትን የተላበሰ የዲጂታል ኢኮኖሚ በመገንባት እና የቴክኖሎጂ ባለቤትነትን በማረጋገጥ የአፍሪካን ብልጽግና ማረጋገጥ ይቻላል ሲሉ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ሶካ ገለጹ።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ሶካ ከአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ዋና ዳይሬክተር ፋታላህ ሲጂልማሲ ጋር ተወያይተዋል።

ውይይታቸው የቴክኖሎጂ ባለቤትነትን ማረጋገጥ በሚቻልበት አጀንዳ ዙሪያ ያተኮረ እንደሆነም ተመላክቷል፡፡

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር(ኢመደአ) ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ሶካ ከአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ዋና ዳይሬክተር ፋታላህ ሲጂልማሲ ጋር ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘውም አፍሪካዊ ማንነትን የተላበሰ የዲጂታል ኢኮኖሚ በመገንባት እና የቴክኖሎጂ ባለቤትነትን በማረጋገጥ የአፍሪካን ብልጽግና ማረጋገጥ ይቻላል ብለዋል፡፡

ኢመደአ እንደ ተቋም በቴክኖሎጂ ባለቤትነት እና በዲጂታላይዜሽን ዙሪያ ያካበተውን አቅም፣ ልምድና እውቀት ለሌሎች የአፍሪካ ሃገራት አቻ ተቋማት ለማካፈል ዝግጁ ነው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡


 

የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ዋና ዳይሬክተር ፋታላህ ሲጂልማሲ በበኩላቸው የሁሉንም የአፍሪካ ሃገራት አቅምና ተሞክሮ በመደመር አፍሪካዊ የቴክኖሎጂ ባለቤትነትን ማረጋገጥ እንደሚገባ ገልጸዋል።

አፍሪካ የቴክኖሎጂ ባለቤትነትን ማረጋገጥ እና ከውጭ የቴክኖሎጂ ጥገኝነት መላቀቅ እንደሚገባትም ጨምረው አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ተሞክሮ ለሌሎች የአፍሪካ አገራት ጥሩ ምሳሌና መነሻ ሊሆን እንደሚችል መግለጻቸውን ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

የኮሚሽኑ ዋና ዳይሬክተር አያይዘውም በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የተመለከቷቸው አገር በቀል የቴክኖሎጂ ምርትና አገልግሎቶች ወደ ሌሎች የአፍሪካ ሃገራት መስፋፋት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡

የሁሉንም የአፍሪካ ሃገራት አቅምና ተሞክሮ በመደመር አፍሪካዊ የቴክኖሎጂ ባለቤትነትን ማረጋገጥ እንደሚገባም ነው የተናገሩት፡፡

ከውይይቱ በተጨማሪ አቶ ሰለሞን የአስተዳደሩን የዲጂታል ኤግዚቢሽን እና የታለንት ልማት ማዕከሎች ለኮሚሽኑ ዋና ዳይሬክተር ማስጎብኘታቸውም በመረጃው ተጠቅሷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም