የክረምት የስፖርት ሥልጠና ሥነ-ልቦናን ከመገንባት ባለፈ ማኅበራዊ ግንኙነትን ለማሻሻል ይረዳል - አሰልጣኞችና ሰልጣኞች - ኢዜአ አማርኛ
የክረምት የስፖርት ሥልጠና ሥነ-ልቦናን ከመገንባት ባለፈ ማኅበራዊ ግንኙነትን ለማሻሻል ይረዳል - አሰልጣኞችና ሰልጣኞች
አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 20/2015 (ኢዜአ) ፦ በክረምት የስፖርት ሥልጠና መሳተፍ ጊዜን በአግባቡ ለመጠቀም፣ ሥነ-ልቦናን ለመገንባትና ማኅበራዊ ግንኙነትን ለማሻሻል እንደሚረዳ አሰልጣኞችና ሰልጣኞች ገለፁ።
ስፖርት ማንኛውንም ዜጋ በተለይም ሕፃናትንና ወጣቶችን በሥነ-ምግባር በማነፅ መልካም ትውልድ እንዲፈራ በማድረግ ረገድ የማይተካ ሚና እንዳለው እሙን ነው።
ሁሉም ሰው በሚሰራበትም ሆነ በሚኖርበት አካባቢ በተናጥልም ይሁን በቡድን በተለያዩ የስፖርት እንቅስቃሴዎች በመሳተፍ አብሮነቱንና ጤንነቱን ያዳብራል።
በዚህ ረገድ በተለይም በክረምት ወቅት ለታዳጊዎችና ወጣቶች የሚሰጡ የስፖርት ሥልጠናዎች ተጠቃሽ ናቸው።
በክረምት የስፖርት ሥልጠና ጉልህ ሥፍራ ከያዙ የስፖርት ዓይነቶች መካከል የቴኳንዶና የቦክስ ስፖርት ይጠቀሳሉ።
በኢንተርናሽናል ቴኳንዶ የስድስተኛ ዳን ባለቤት የሆነው ኢንስትራክተር ኤልያስ ኩመል፤ ሰዎች በርካታ ወጣቶች በተለይም በክረምት ወቅት ትኩረት ሰጥተው ስፖርት እንደሚሰሩ ይናገራል።
የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች መበራከት ወጣቶች ከአልባሌ ቦታ እንዲርቁና በሥነ-ምግባር እንዲታነፁ ያደርጋል የሚለው ደግሞ በኦሜድላ የስፖርት ክለብ የቦክስ አሰልጣኝ የሆነው መኮንን ጌታቸው ነው።
በቦክስ ስፖርት አገሪቱን በተለያዩ መድረኮች የሚወክሉ ተወዳዳሪዎችን ለማፍራት የክረምት ሥልጠና የማይተካ ሚና እንዳለው አሰልጣኝ መኮንን ጠቁሟል።
የኢንተርናሽናል ቴኳንዶ የሦስተኛ ዳን ባለቤት የሆነው እስማኤል ሙባረክ የቴኳንዶ ስፖርት በአካልና በአዕምሮ ዝግጁ እንደሚያደርግ ይናገራል።
በስፖርቱ መልካም ባህሪ ማምጣት ስለሚቻል ወላጆች ልጆቻቸውን የክረምት ስፖርት ባለበት አካባቢ ሁሉ በመላክ እንዲሳተፉ ማድረግ ተጠቃሚ ያደርጋቸዋል ብሏል።
የቴኳንዶ ስፖርት ለተለማማጇ ቃልኪዳን ፈለቀ ስፖርት መሥራቷ በራስ መተማመኗን ከፍ እንዳደረገላት ትናገራለች።
ስፖርት ሥነ-ምግባርን ከማነፅ ባለፈ አካልን የሚገነባ በመሆኑ ወላጆች ልጆቻቸውን በስፖርት እንቅስቃሴዎች ማሳተፍ አለባቸው ብላለች።
በኦሜድላ ስፖርት ክለብ በ51 ኪሎ ግራም የቦክስ ስፖርት ተወዳዳሪ የሆነው ፍትዊ ጥዑማይ በበኩሉ፤ የሚሰራው የቦክስ ስፖርት ችሎታና ጥበብን እንደሚፈልግ ይናገራል።
በክረምት ደግሞ እንደ ቦክስ ያሉ ስፖርቶች ቢሰሩና ስፖርታዊ ውድድሮች ቢበራከቱ ሕብረተሰቡ ወደ ስፖርት እንደሚሳብ ይገልፃል።
የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዳዊት ትርፉ፤ የክረምት የስፖርት መርሃ-ግብር ሁሉም ሰው ያለፈበትና በመገናኛ ብዙኃን ጭምር እየታገዘ የልጆች አዕምሮ ላይ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።
በክረምት የስፖርት መርሃ-ግብር መሳተፍም ልጆች ስለ አካባቢያቸው በቂ ዕውቀት እንዲኖራቸው እንደሚያስችልም ተናግረዋል።
ወጣቶች በተለያዩ ስፖርታዊ መርሃ-ግብር እንዲታቀፉና አምራች ኃይል እንዲሆኑ ለማድረግ ቢሮው በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።