የሩቅ ቅርቧ ሞስኮ!

(በአየለ ያረጋል)

 

 

 

ወትሮን ከዘንድሮ ያዋደዱ ሰማይ ታካኪ ሕንፃዎች መካከል ነው። እንደ ባሕር የተዘረጋው አርበ-ሰፊ ወንዝ እንደ ዝናር እየዞረ ይጥመለመላል። አይነተ ብዙ አያሌ ጀልባዎች በወንዙ ላይ ተሳፍረው ይርመሰመሳሉ። ሰዎች ደግሞ በጀልባዎቹ ተሳፍረው የወደዱትን ዕህል ውሃ እየተቋደሱ ይጓዛሉ። በወንዙ ግራ ቀኝ የሚገኙ ጥቅጥቅ ደን የሚመስሉ ዛፎች ሐመልማላዊ ገጽታ ለስፍራው ልዩ ውበት ደርቦለታል። ከላይ የመኪና፣ ከስር ፈጣን ባቡርን የሚሸከም ግዙፍ ድልድይ በወንዙ ላይ ተዘርግቷል። ከወንዙ ሰማይ ላይ የኬብል መኪናዎች ይከንፋሉ። የሰዎች የሐሴት ጥግ ይነበባል። ትዕይንቱ በወፍ በረር ዕይታ ሲቃኝ ዕፁብ ድንቅ ነው። ተለምዶ ከተፈጥሮ ተዛምዶ ሲታይ በአግራሞት ዕጅን በአፍ ያስጭናል። ይህ ውበት ያለው የሩቅ ቅርቧ ሩስያ ርዕሰ መዲና ሞስኮ ነው። ወንዙም ሞስኮቫ ነው!

ሞስኮ አምባ ላይ ነኝ-መሀል ከተማ። ሁሉም ወለል ብሎ በሚታይበት አምባ ላይ በተተከለው አጉሊ መነፀር ሞስኮን እስከ ዕይታ አድማሷ በቀላሉ መቃኘት ይቻላል። የአያሌ ክፍል ዓለማት ስፍር ቁጥር አልባ ጎብኝዎች ስፍራው ላይ የተኮለኮሉት ለዚህ መሆኑ ነው። እኔም ወጉ ደርሶኝ ሞስኮቫ ወንዝ ራስጌ ተገትሬ ነገረ ሞስኮን ኪነ-ሕንፃ፣ ኪነ-ውበት፣ ስነ-ታሪክ መቃረም እና ሀሳብ ማውጠንጠን ቻልኩ።

በሞስኮ ሰማይ ስር፤ ከሞስኮ አምባ በስተሰሜን ምዕራብ ክሬምሊን ቤተ መንግስት ግርማውን ተላብሷል። ብርቱ ውሳኔዎች መጸነሻና መወሰኛ ቁልፉ ቦታ-ክሬምሊን። ከክሬምሊን በስተቀኝ በኪነ ሕንፃው የሚወደሰው ባለወርቃማ ዕንቁላል መሰል ጉልላት የተጌጠው ቅዱስ ቤዚል ካቴድራል ይታያል። ከቀዩ አደባባይ ራስጌ! እነሆ ከሩቋ የሕልሜ ከተማ በአካል ተገኝቼ ሁለንተናዊ መልኳን በስሱ እየቃኘሁ ነው።

አጋጣሚዎች የመንደር መፃዒ ዕድል ይወስናሉ-እንደ ሞስኮ። የግዙፉ ግዛተ-አፄ ሩስያ ርዕሰ መዲናነት ከታሪካዊቷ ቅዱስ ፒተርስበርግ ወደ ሞስኮ የዞረው ከአንድ ምዕተ ዓመት በፊት በፈነዳው አብዮት አጋጣሚ ነበር። አብዮቱ ለሀገሪቷ ብቻም ሳይሆን ለዛሬዋ ሞስኮም አብዮት ወለደ።

ሞስኮ ከተቆረቆረች 876 ዓመት ሆኗታል። በ1147 ነበር ምስረታዋ። ስሟም እንደ መቀነስ በታጠቃት ’ሞስኮቫ’ ወንዝ የተወሰደ ነው። በሂደት ሞስኮ መባሏን አስጎብኚዎቼ አጫውተውኛል። ክሬምሊን የሞስኮ አስኳል ነው። ትርጓሜውም የከተማ ውስጥ ምሽግ ማለት ነው። የሩስያ መዲናዋ ሞስኮ ከክሬምሊን ምሽግ ተነስታ ለዘጠኝ ክፍለ ዘመናት ተጉዛለች። ሞስኮ የሮማን ግዛተ-አጼ ዘመነ መንግስትን ስነ መለኮታዊ፣ ስነ መንግስታዊና ባህላዊ አሻራዎችን በማስቀጠሏ በታሪክ ሊቃውንት ዘንድ ከሮማን እና ከኮንስታንቲኖፕል ስልጣኔ ቀጥሎ  ‘ሳልሳዊት ሮም’ የሚል ተቀጽላ ስም ተችሯታል።


 

ከሞስኮ ውብ መልኮች መካከል ‘ሰባቱ እህትማማቾች’ (The Seven Sisters) ይጠቀሳሉ። በኪነ-ሕንጻ ጥበባቸው የሚያስደንቁ ሰባት ቦታ ላይ የተገነቡ ሰባት ሰማይ ጠቀስ ሕንጻዎች ናቸው። ከአስጎብኚዎቹ እንደተረዳሁት ሕንጻዎቹ በታላቋ ሶቬት ህብረት በዘመነ ዮሴፍ ስታሊን ከ1947 እስከ 1953 (እ.አ.አ) በአራት ዓመታት ብቻ የተገነቡ ናቸው። በወቅቱ በአውሮፓ ረጅም ሕንጻዎች ነበሩ።  ትዕምርታቸውም የሶሻሊስት ርዕዮተ ዓለም ዘላለማዊነት መጠቆም ነበር። በርግጥም ዛሬም የሶቬት ሕብረት ጉልህ አሻራዎች ናቸው። ዛሬም የሚሰሩ በርካታ ኪነ-ሕንፃዎች እህትማማቾችን ለመምሰል ይጥራሉ። ሰባቱ እህትማማች ለተለያዩ ተቋማት ቢሮነት፣ በአፓርታማነት እና በሆቴል አገልግሎት እያገለገሉ ይገኛሉ። ለአብነም በ1755 የተመሰረተው ስመ ጥሩ የሞስኮ ስቴት ዩኒቨርሲቲ፣ የሩስያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ሌኒንግራድስኪያ (ሒልተን ሞስኮ) እንዲሁም ዩክሬን ሆቴል (ዛሬ ራዲሰንብሉ ሞስኮ) በእህትማማቾች ሕንጻዎች ላይ ይገኛሉ።

ከሞስኮቫ ወንዝ ባሻገር ሉዥንኪ ኦሎምፒክ ኮምፕሌክስ ከነሞገሱ ይታያል። ስቴዲየሙ በ2018 ሞስኮ የፊፋ ዓለም ዋንጫ ስታስተናግድ ቁልፍ ሚና ነበረው። ከስቴዲየሙ ባሻገርም 72 ሜትር የሚረዛዝሙ ወርቃማ ሚናሮዎች የተጌጠው የሞስኮ ካቴድራል መስጊድ ይስተዋላል።


 

መልክዓ-ሞስኮ ትዕይንቶች ለዕይታ አይሰለቹም። በሞስኮቫ ታሪካዊና ባለግርማ ሞገስ ድልድዮች፣ የቀዳማዊ ፒተር(ታላቁ ፒተር) ሰማይ ጠቀስ ሐውልት፣ ጎርክና መሰል ሰፋፊ የመሃል ከተማ ፓርኮች፣ ወጥ ከፍታ ያላቸው ውብ መኖሪያ ሕንጻዎች… ብቻ መልከ-መልካም ናት።

ሩስያ በ20ኛው ከፍል ዘመን መባቻ የሶቫሊዝም አብዮት ከመፈንዳቱ በፊት በቄሳሮች (ጻሮች) በሚመራ ዘውዳዊ ስርዓት ለዘመናት ተዳድራለች። የፈረንሳይ መሪ ናፖሊዎን ቦናፓርት ሞስኮን በአንድ ወቅት በቁጥጥር ስር አድርጓት እንደነበር አስጎብኚዎች ይናገራሉ።

በ17ኛው ክፍለ ዘመን የነገሰው ቀዳማዊ ፒተር (ቀዳማዊ ጴጥሮስ) የሁሉም ሩስያ መስራች እና የመጀመሪያው አጼ ነው።  የዘመናዊት ሩስያ መሀንዲስ ተደርጎ ይወሳል። ከቀዳማዊ ፒተር እስከ ዳግማዊ ኒኮላስ የሩስያ አፄዎች ዋና ቤተ መንግስት ቅዱስ ፒተርስበርግ ነበር። ድሕረ አብዮት የመንግስት መቀመጫ ሞስኮ ሆነች።

አሁናዊ ሞስኮ በከተማ መሰረተ ልማቷና ስርዓቷ ከዓለማችን ውብ ከተሞች አንዷ ናት። የሩስያ ታሪክ ማዕከል፣ የቢሊየነሮች መደብር፣ የዝነኛ ጠቢባን፣ ሳይንቲስትና ታዋቂ ሰዎች መገኛም ናት። በመሰረተ ልማት እና በኑሮ ጥራቷም በፈረንጆቹ 2022 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከዓለማችን ምርጥ ግዙፍ ከተሞች መካከል በምርጥነት መርጧት ነበር። ሞስኮ ከ13 ሚሊዮን ህዝብ በላይ በመያዝ በህዝብ ብዛቷ ከዓለም ስምንተኛዋ ከተማ ናት።

ምስጋና ለኢንተራሺያ (InteRussia Program 2023) የኢንተርሽፕ ስልጠና ይሁንና የሩቅ ቅርቧን ሞስኮ በቅጡ ተዘዋውሮ የመጎብኘት፣ ከጥበብ ድግሷ የመቋደስ፣ በውበቷ የመመሰጥ፣ ከታሪኳ የመቃረም ዕድል አገኘሁ። የሩስያው ዜና አገልግሎት ‘ስፑትኒክ’ ከአጋሮቹ ጋር ባመቻቸው በዚህ ፕሮግራም ከአፍሪከ ሀገራት 10 ወጣት ጋዜጠኞች ተሳትፈናል። እኔ ከሌሎች በተለየ ለሩስያ ቀረቤታ ያለኝ ያህል ይመስል ነበር። ምክንያቱ ደግሞ የታላቁ ሩስያዊ ደራሲ አሌክሳንደር ፑሽኪን ቅድመ አያት በቀዳማዊ ፒተር ዘመን በጀግንነቱ በተመለመለው አብርሐም ሃኒባል ኢትዮጰያዊ መሆኑ ነው። በርግጥም ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ከሩስያ ጋር ያላቸው ታሪካዊ ግንኙነት በ1960ዎቹ የተጀመረ ሲሆን የኢትዮጵያ ግን ብዙ ዘመናት ወደኋላ ይርቃል። ሩስያን በስማበለው የመናፈቅ ጠኔም ነበረብኝ።


 

ለምን ሩስያን ለማየት ናፈቅሁ?

 

ከታሪካዊ አጋጣሚዎች ተነስቼ ለሩስያ አወንታዊ ስሜት ካደረብኝ ውሎ አድሯል። በዘመናት ሸለቆ በዘለቀ የኢትዮ- ሩስያ ጽኑና ጥልቅ ወዳጅነት እና የሁለቱ ሀገራት የታሪክ ሂደቶች ተመሳስሎሽ ጥቂት ግንዛቤ ነበረኝና።

ሁለቱ ጥንታዊ ሀገራት በዘውዳዊ ስርዓት (ሩስያ በቄሳር፤ ኢትዮጵያም በአጼዎች) ለዘመናት ተዳድረዋል። በየዘመናቱ አያሌ ኅይሎች ሁለቱንም ሀገር በተደጋጋሚ አጥቅተዋል። በአንድ ክፍለ ዘመን ውስጥ (ዓመቱ ቢለያይም) የሁለቱ ሀገራት ባላባታዊ ስርዓት በስር ነቀል አብዮት ተገርስሷል። አብዮቱ የንጉሳዊያን ቤተሰቦችን ለስደትና ለጉዳት በመዳረግ ተመሳሳይ ዕጣ ፈንታ አድርሷል። ድሕረ አብዮት የእርስ በርስ ደም አፋሳሽ ዕልቂት ሩስያ በቦልሸቪክ እና መንሸቪክ (Bolshevik and Menshevik)፤ ኢትዮጵያ ደግሞ በቀይና ነጭ ሽብር መልከ ብዙ ግፎች አስተናግደዋል።

የሁለቱ ሀገራት ነገስታት ግንኙነት ለመመስረት ፅኑ መሻት እንደነበራቸው ይወሳል። ቀዳማዊ ፒተር ወደ ኢትዮጵያ መልክተኛ ለመላክ ሞክሮ እንዳልተሳካለት ይወሳል። ከኢትዮጵያ ወገንም ዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ ታሪካዊ የ’ሴቫስቶፖል’ መድፍን ስያሜ የሰጠው በክርሚያ ጦርነት መነሻ ነበር። አጼ ዮሐንስ አራተኛ በተመሳሳይ በተለይም ከክርስትና እምነት ጋር በተያያዝ ከሩስያ ጋር ጥብቅ ወዳጅነት ለመመስረት ፍላጎት እንደነበራቸው ይወሳል።


 

በመጨረሻም በ19ኛው ክፍል ዘመን መገባደጃ በዳግማዊ አጼ ምኒልክ እና በቄሳር ዳግማዊ ኒኮላስ ዘመነ መንግስት ይፋዊ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ተወጥኗል። በተለይም በ1880ዎቸ መጨረሻ ማሽኮቭ፣ ኤሊሴቭና ሌዎንቴቭ፣ አሌክሳንደር ቭላቶቪችና መሰል ሩስያዊ ተጓዦችና የስነ መልክዓ ምድር አጥኝዎች ወደ ኢትዮጵያ መምጣት የሀገራቱን ግንኙነቱን ፈር አስይዟል። የኢትዮጵያና የሩስያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት ትብብርም በ1880ዎቹ ጀምሮ እየተጠናከረ መምጣት ለባህል ዲፕሎማሲው የማይናቅ ሚና ነበረው። በአድዋ ድል ማግስት በ1897(እ.አ.አ) ሩስያ ኤምባሲዋን አዲስ አበባ ከፈተች።

በ1895(እ.ኤ.አ) ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ምድር ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሩስያ የዲፕሎማሲ ልዑክ በፊታውራሪ ዳምጠው ከተማ (የራስ ደስታ ዳምጠው አባት እና በኋላም በአድዋ ጦርነት የተሰዉ) የተመራ ልዑክ ልካለች። ፊታውራሪ ዳምጠው የሩስያ አጼዎች መናገሻ በሆነችው ቅዱስ ፒተርስበርግ ሲደርሱ ደማቅ መስተንግዶ ተደርጎላቸው ለአንድ ወር ቆይተው ቀጣይ ግንኙነት መሰረት መጣል ብቻ ሳይሆን ለአድዋ ጦርነት ወሳኝ ድጋፍ ሰንቀው ተመልሰዋል። በኋላም በኒኮላይ ሌዎንቴፍ (በኋላ ደጃዝማች) መሪነት አድዋ ጦርነት ላይ አይተኬ ሚና የተጫወቱ ከ40 በላይ የቀይ መስቀል በጎ ፈቃደኞች እንዲመጡ አስችሏል። በበርሊኑ ጉባዔ መላው የአውሮፓ ኅያላን አፍሪካን ለመቀራመት ሜዴትራኒያንን ሲያቋርጡ ሩስያ ግን በተዘዋዋሪም ቢሆን ከኢትዮጵያ ጎን ቆማ ደገፋለች። ይህ የሩስያ ቀዳሚው ውለታ ነበር።

አጼ ምኒልክ በአውሮፓዊያኑ 1898 በፒዮተር ቫስሎቭ የሚመራ የሩስያ ልዑክ ደማቅ አቀባበል አደረጉ። ጄኔራል ኮንስታንቲን ሊሸን የተባሉት በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የሩስያ አምባሳደር (በወቅቱ ካውንስለር) አዲስ አበባ ውስጥ ሕይወታቸው እስኪያለፍ ድረስ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት በጸና መሰረት ላይ እንዲቀጥል አይተኬ ሚና ተጫውተዋል። መካነ ቀብራቸው አዲስ አበባ ይገኛል።

በርግጥ የዳግማዊ ምኒልክ እና የዳግማዊ ኒኮላስ ግንኙነት ሙሉ መተማመንና ልባዊ ወዳጅነት እንደነበረው የተለዋወጧቸው ደብዳቤዎች ዋቢ ናቸው። የደስታና ሀዘን ስሜቶችን ተጋርተዋል። ለአብነትም ዳግማዊ ኒኮላስ በራስ መኮንን ድንገተኛ ሕልፈት ማዘናቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ ልከዋል። በተመሳሳይ ዳግማዊ ምኒልክ በጦርነት በሩስያዊያን ላይ የደረሰ ጉዳትን አስመልክቶ በጀኔራል ሊሸን በኩል የማጽናኛ ሀዘናቸውን ልከዋል። ሀዘን ብቻም ሳይሆን ተጎጂዎችን ለመደገፍ በሚል ለሩስያ ቀይ መስቀል ገንዘብ ድጋፍ ልከዋል። ‘የአጼ ምኒልክ የውጭ ሀገር ደብዳቤዎች’ በተሰኘው የጳውሎስ ኞኞ መጽሐፍ እንደተጠቆመው ዋና ፍሬ ነገሩ ይነበባል።

 “ሰላም ላንተ ይሁን፡፡ በሩቅ አገር የመስኮብ መንግሥት ልጆች ለንጉሣቸውና ለአገራቸው ደማቸውን በማፍሰሳቸው ብዙ አሳዘኑኝ፡፡ ጥቂትም እንኳን ቢሆን ለእነዚያ ለተጐዱት ልጆች ለመርዳት ብዬ ከዚህ ደብዳቤ ጋር አንድ አክሬዲልዩን ቼክ ስለመቶ ሺ ፍራንክ ልኬልሃለሁና ይህንን ቼክ ከመልካም ምኞቴ ጋር ለመስኮብ የቀይ መስቀል አለቃ እንድታደርስልኝ ይሁን።ይህን አሁን በመስኮብ መንግሥት የተነሳውን ጦር ጠላታቸውን አሸንፈው በቶሉ እንዲያልቅ እጅግ የከበሩ ታላቅ ወዳጃችን የመስኮብ መንግሥት ንጉሠ ነገሥት በጤና በሀብት እንዲያኖራቸው፣ለመስኮብ መንግሥት ሰላምና ረፍት እንዲሰጥ እግዚአብሔርን እንለምናለን”፡፡

የሁለቱን ሀገራት መልክዓ ምድራዊ ርቀት ያልገደበው መተሳሰብ ስሜት ያንጸባረቀ፤ የጋራ ዕጣ ፈንታ እንዳላቸውም የሚያመላከት ይመስላል። አጼ ምኒልክ ከሩስያ በስተቀር ኢትዮጵያ ሁነኛ ወዳጅ እንደሌላት እስከ መግለጽ ደርሰው ነበር። ይህ የኢትዮ-ሩስይ ወዳጅነት እስከዛሬ ሳይዛነፍ በመልካም ትብብርና መደጋገፍ ቀጥሏል። ሩስያዊያን ደጃዝማች ባልቻ ሆስፒታልን ጨምሮ በተቋማት ግንባታ አሻራቸውን አሳርፈዋል።

በሁለተኛው የፋቪስት ኢጣሊያ ወረራ ወቅትም በኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ ሲጣል የተቃወመች ሩስያ (የወቅቱ ሶቬት ህብረት) ነበረች። ከነጻነት በኋላም በሶቬት ህብረት ሩስያና ኢትዮጵያ ወዳጅነት ዳግም ተጠናክሯል። በአጼ ኅይለስላሴ ዘመነ ምነግስት በሰው ሀብት ልማትና መሰረተ ልማት ላይ መልካም የትብብር ጅምሮች ነበሩ። በዘመነ ደርግ ደግሞ ከፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ጋር ተዳምሮ ሁሉን አቀፍ ትብብር ነበር። በዘመኑ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት መጠበቅ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል። ከ20 ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያን በቀድሞዋ ሶቬት ህብረት ዘመን የነጻ ትምህርት ዕድል አግኝተው ትምህርታቸውን ተከታትለዋል።


 

እነዚህ ጥልቅ ታሪካዊና መንፈሳዊ ትስስሮች ሩስያን እንድናፍቅ ያደርገኛል። በሌላ በኩል ስለሩስያ ትልቅ ክብር እንዲኖረኝ ያደረገኝ በቁንጽል ንባቤ እንዲሁም በየዘመናቱ ሩስያ የተማሩ ኢትዮጵያዊያን ስለሩስያ የሚሰጡት ፍቅርና አክብሮት ነበር።

ለአብነትም ፊታውራሪ ተክለሐዋሪያት ተክለማርያም ይጠቀሳሉ። በራስ መኮንን ቤት ያደጉት ፊታውራሪ ተክለሀዋሪያት ገና በልጅነታቸው (በ19ኛው ክፍል ዘመን መጨረሻ) በራስ መኮንን አደራነት እንዲማሩ በሚል ከአንድ ሩስያዊ ጋር ወደ ቅዱስ ፒተርስበርግ አቅንተው ያደጉ፣ የተማሩና የኖሩ እንዲሁም በኋላ በዘመናዊት ኢትዮጵያ ፖለቲካና ሀገር መንግስት ግንባታ ሂደት ትልቅ ሚና የነበራቸው፣ ከቀደምት ዘመናዊ ትምህርት ፈር ቀዳጆች መካከን የሚጠቀሱ ጉምቱ አሰላሳይ ምሁር ሰው ናቸው። በሩስያ እናቶች ቤት ያደጉት እነሁ ሰው ‘አውቶባዮግራፊ’ በተሰኘው ግለ ታሪክ መፅሐፋቸው እንደከተቡት ስለሩስያ ህዝብ ፍቅርና የሀገሩ ኅያልነት አንስተው አይጠግቡም። “ሩስያ ሁለኛ ሀገሬ ናት። ለእኔ የዋሉልኝ ውለታ መቼም ልረሳው አልችልም። ሩሲያኖች ሐሳባቸው ሰፊ፣ ሥራቸው ጠንካራ ነው: በማንኛውም ሙያ የሚያሽንፋቸው ኃይል ሊኖር አይችልም"ብለዋል።

የቀድሞ ተማሪዎችም ቢሆኑ ስለሩስያ ህዝብ ያላቸው አክብሮት ልዩ ነው። በሩስያ አይረሴ ትዝታ የቋጠሩበት፣ ወጣትነታቸውን ያጣጣሙበት፣ ታሪክ፣ ስነ ጥበብና ስነ ጽሁፍ ከፍታቸው የሚደንቃቸው፣ የሀገር ፍቅር ስሜታቸው የሚያስቀናቸው ናቸው። ካነጋገርኳቸው መካከል ደራሲና ሃያሲ አያልነህ ሙላቱ፣ አንጋፋው ዲፕሎማት በላይ ግርማይ፣ የእርሻ ባለሙያው አለማየሁ አሊ እና ዕውቁ ሰዓሊ መዝገቡ ተሰማ የሩስያ አየር ጸባይ ፈተናን ባይዘነጉም የሰዎችን ፍቅር፣ የሀገሩን ጥበብና ኅያልነት ግን አውስተው አይጠግቡም። ዛሬም ይናፍቃቸዋል።

የተናፋቂዋ ሞስኮ ልዩ መልኮች

 

የሚዲያ ትርክቶች እና የሞስኮ ዕውነታ

ሞስኮ ከመምጣቴ ጥቂት ቀናት በፊት ዋግነር ቅጥረኛ ወታደሮች ሞስኮን ሊቆጣጠር እያመሩ ነው፤ የመንግስት ወታደሮችም በሞስኮ ጎዳናዎች እየተውረበረቡ ነው የሚለው ዜና የምዕራባዊያን ሚዲያዎች ሰበር ወሬ ነበር። ከአዲስ አበባ-ዶሞዴዶቮ አየረ ማረፊያ ደርሼ፣ ወደ ማረፊያ ሆቴል ሳመራ ያየሁት መልክ የጠበቅሁት አልነበረም። ወሬና ዕውነታው ፍጹም የተለየ ነበር። በሞስኮ ጎዳናዎች ቅንጡ ተሽከርካሪዎች፣ ጥቅጥቅ ጫካ የሚመስሉ ዛፎች፣ ቆነጃጅት ልጃገረዶች እንጂ ወታደር አልነበረም። (ከዚያም በኋላ አላየሁም)። ይልቁኑም በዕለቱ የገጠር ሰዎች (አርሶ አደሮች) ለመዝናናት ወደ ከተማ እየመጡ በመሆኑ ሞስኮ የቅንጡ መኪኖች ትራፊክ መጨመሩን ሰምቼ፤ የሀገሬን አርሶ አደር ሕይወት ሀሳብ አቃጭሎብኝ በቁጭት አስፈግጎኛል።

የሞስኮ መልክና የመጀመሪያ ግምት ልዩነት የእኔ ብቻ ሳይሆን የሌሎች አፍሪካዊያን ጓዶቼም ትዝብት ነበር። የዚምባብዌ ፕሬስ ድርጅት ጋዜጠኛ ሞቢሌ ችሊ ለረጂም ዓመታት በተለያዩ የምዕራባውያን የቴሌቪዥን መስኮቶች ስለሩስያ የሰማሁት ነገር አሉታዊ ነበር። በአካል ሩስያ መጥቼ ያረጋገጥኩት ነገር ቢኖር ግን የሩስያዊያን በጎ ማንነታቸው አለመተረኩም ነው” ይላል።

የሞስኮ ሰላማዊነትና የንግድ ማዕከላት ድምቀት ጦርነት ውስጥ ያለች ሀገር አትመስልም። ‘እውን በሁለንተናዊ ማዕቀብ ያለች ሀገር ናት’ አሰኝቶኛል። የሶስት ሳምንታት ቆይታዬ ሞስኮ ቱሪስቶች መነሃሪያ መሆኗን ታዝቢያለሁ። በየመዝናኛ ቦታዎችና ታሪካዊ ስፍራዎች የሚርመሰበስ የተለያዩ ሀገራት ጎብኚዎች ብዛት የትየለሌ ነው። የአንድ ወገን የዓለም የሚደያ ቅኝት ወደ ብዝሀ ድምጽ ዓለም መለወጥ የሚሻበት ወቅት መሆኑን አፍሪካዊያን ጓደኞቼ ሲነግሩኝ ነበር።

ተዓምረኛዋ ሞስኮ

መልክዓ-ሞስኮ አጃይብ ነው። ‘አዲስ እረኛ’ እንዲሉ ከተማዋ ከመግባቴ በከተማዋ ስልጣኔ በመደመም ያስደነቀኝን ነገር ሁሉ በፎቶ ለማስቀረት እየሞከርኩ ነበር። ጠለቅ ባልኩ ቁጥር ግን አግራሞቴ እየጨመረ መጣና ሰለቸሁ። በየዕለቱ የሚወለወሉ ጎዳናዎች፣ የኪነ ሕንፃ ጥበብ የፈሰሰባቸው አፓርታማዎች፣ በየፊናው የሚስተዋሉ ታሪካዊ ስፍራዎች፣ ድልድዮች፣ አዕዋፍት የሚርመሰመሱባቸው አረንጓዴ ስፍራዎችን ያስቀናሉ።

ሞስኮ ተፈጥሮን፣ ታሪክን፣ ትውፊትንና ስነ ጥበብን አሰናስላ ያቃፈች ከተማ ናት። የምድራዊ ገነት ሽርፍራፊ ሳትሆን አትቀርም። አያሌ ታሪካዊና ውብ ከተሞች ሊኖሩ ቢችሉም እንደሞስኮ በተፈጥሮ የታደለ፣ በታሪክ የከበረ፣ በጥበብ የተቸረ ኩሉ በኩለሔ አይነት ከተማ ማግኘት ሊያዳግት ይችላል። ሞስኮ የሩስያ የባህል ሙዳይ፣ ሞስኮ የስነ ጥበብ ማዕከላት ማህደር፣ የቅርስና ታሪክ ቤተ መዘከር፣ የፖለቲካና የምጣኔ ሀብት ማዕከል ናት። ሞስኮ በስርዓትና በቅጥ የተገነባች፣ በመገንባት ላይም ያለች፣ ትናንቷን በቅጡ የምትዘክርና የምታድስ ከተማ ናት።

ዕጹብ ድንቅ ኪነ ሕንጻ ጥበብ ያላቸው የሞስኮ አብያተ ክርስቲያናት ብዛት ይገርማል። የቀዩ አደባባይ ወርቃማ ሽንኩርት ቅርፅ ጉልላት ተምሳሌትነት የያዙ አብያተ ክርስቲያናት የሞስኮ ድምቀት ናቸው። በየስጦታ ዕቃ ቤቶች እንደ ብሔራዊ ትዕምርትነት ይሸጣሉ።

ኪነ ጥበብ እና ሩስያ በታሪክ ዘውድ እና ጎፈር ይመስላሉ። በ10ኛው ከፍለ ዘመን ክርስትና እምነት መስፋፋትን ተከትሎ መፋፋት የጀመረው የሩስያ ኪነ ጥበብ በቀዳማዊ ፒተር ዘመን ጀምሮ ያለማቋረጥ እምርታ እያሳየ ቀጥሏል። እናም በዘመናት የሩስያ ኪነ ጥበብ ቱርፋቶች ከመላው ዓለም የጥበብ ቤተሰቦችና ጎብኚዎችን መስህብ ሆነዋል። ሩስያዎች ደግሞ ታሪካቸውንና ባለታሪኮችን ያከብራሉ፤ በቅጡም ይዘክራሉ።

ካስነደቁኝ የሞስኮ የኪነ ጥበብ ማዕከላት መካከል ትሬትያኮቭ ጋለሪ (Tretyakov Gallery) አንዱ ነው። 11ኛው እስከ 20ኛው ክፍለ ዘመን የነበሩ  ከ180 ሺህ የሩስያ ስዕላት፣ ቅርጻ ቅርጾችና ግራፊክ ስራዎች የሩስያ የስነ ጥበብ ስራዎችን ያቀፈ ተቋም ነው።  አስጎብኚዎቹ እንደሚሉት ጋለሪው ከ150 ዓመታት በፊት ፓቬል ትሬትያኮቭ በተባለ አንድ ባለጸጋ የስዕል ስብስቦች ቤት የነበረ ሲሆን በኋላ በባለቤቱ ፈቃድ ለመንግስት ተላልፎ የሩስያ የስዕል ጥበብ ማህደርነት ተደራጅቶ የዛሬውን ቅርጽ ይዟል። ጋለሪው የሩስያን ጥንተ ነገር፣ የሶቫሊስት እሳቤን፣ ተፈጥሮን፣ ስነ መለኮትን እንዲሁም ነገን በሚተነብዩ ጠቢባን የተሰሩ ኦርጅናል ስራዎች አቅፏል።

የመላው ሩስያዊያን ኤግዚቪሽን ማዕከል (All Russian Exhibition of Achievements of National Economy) ሌላው አጃይብ ያሰኘኝ ተቋም ነው። በ1940ዎቹ የተገነባ በስፋት፣ በግንባታ ጥራትና ስነ ውበት ለመግለጽ ቃላት የሚያንስበት ማዕከል ነው። የቀድሞዋ ሶቬት ሕብረት ታሪክና ባለታሪኮች፣ የሀገሪቷን የቴክኖሎጂ ምጥቀት ቁልጭ ብሎ ይታያል። የሩስያ የሥነ ሕዋ ቤተ መዘከርም ከዚሁ ማዕከል ፊት ለፊት ይገኛል። ለዚህም ይሆናልይህ ስፍራ በጎብኚዎች ማዕበል ሲታመስ የሚውል ነው።

ሞስኮ ዕልቆ መሳፍርት የሌለው የሐውልት ከተማም ናት። በሞስኮ ጎዳናዎች፣ አደባባዮች፣ በኪነ ጥበብ ማዕከላትና በንግድ ማዕከላት አካባቢዎች ሁሉ መልከ ብዙ የቅርጻ ቅርፅ ጥበብ ከፍታን የሚዋጁና ሞገስ ያላቸው ሐውልቶች ማየት ብርቅ አይደለም። ይህም የሥነ ጥበብ ከፍታቸውን ብቻ ሳይሆን የሩስኪዎችን የሀገር ፍቅር፣ ታሪክና ባለታሪክ የማክበርና የመዘከር ጽኑ መሻትን የሚያሳይ ነው። እናም ከሩስያ ሀገረ መንግስት ምስረታ ጀምሮ አሻራ ያላቸው መሪዎች፣ ጠቢባን፣ ሳይንቲስቶችና ምሁራን ስራቸውን የሚመጥን መታሰቢያ ቆሞላቸዋል። በርግጥ ሐውልት ብቻ ሳይሆን በጎዳናዎች፣ በሜትሮ (በከተማ ባቡር) ጣቢያዎች፣ በተቋማት ስም መሰየምም የተለመደ ነው።

የሞስኮ ጎዳናዎች የአዘቦት ትዕይንቶች

መቼስ የጎዳናዎች ስፋት፣ ጥራት፣ ውበት፣ የመሬት ስር እግረኛ ማቋረጫዎች፣ አረንጓዴያማ ተክሎች ለዐይን አይጠገቡም። ዋው! ብሎ ማለፍፍ ይቀላል። ከጎዳናዎች ውበት ባሻገር ግን መሰረተ ልማቱ ከቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን የተቆራኘበት ከፍታ ጥግ ግሩም ነው። ሞስኮ ዲጂታላይዜሽን የአገልግሎትና ንግድ ስራና ኑሮን ያቀለለባት ከተማ ናት። ሞስኮ ውስጥ ከግለሰብ እስከ መንግስት ሕንጻዎች፣ መሰብሰቢያ ስፍራዎች፣ ጎዳናዎች በደህንነት ካሜራ አላቸው። ከ70 በመቶ በላይ የጸጥታ ችግፍ የሚፈታው ካሜራዎች ከቀረጹት ግብዓትን በመጠቀም ነው።

በሞስኮ ጎዳናዎች የሲጋራ ጭስና አጫሽ ማየት አያስደንቅም። ሴትና ወንዱ፣ ወጣትና ሽማገሌ ብሎ በዕድሜና ጾታ ሳይገደብ ያጨሳል። ይህ ወቅቱ ክረምት ስለሆነ (በእነርሱ የፀሐይ ወቅት) እንጂ በበጋ የጭስ ምጣኔው በጣም እንደሚጨምር ሰማሁ። ግን ህዝቡ ስርዓት አለው፤ በማይጨስበት ክልክል ስፍራ ማንም አያጨስም።

በኤሌክትሪክ ኅይል የሚሰሩ አይነተ ብዙ መንቀሳቀሻዎች (ስኮተርና ስኬች)፣ ባይስክሎች እና ሞተርሳይክሎች የሞስኮ መለያዎች ናቸው። የሞስኮ ከተሜዎች አጫጭር ርቀት ለመሄድ ከባስና ሜትሮ(ባቡርይ ይልቅ እነዚህን መንሸራቻዎች ይመርጣሉ። እነዚህ መሳሪያዎች የራሳቸው ፓርኪንግስ ስፍራም አላቸው። ከሌሎች ተከራይቶ ተጠቅሞ መመለስ ይቻላል። በተባበሩት መንግስታት የመሰረተ ልማት ጥራት ተመራጭ ከተሞች መካከል የተጠቀሰችው ሞስኮ፤ ‘የስማርት ሲቲ’ ምሳሌም ሳትሆን አትቀርም።

ሩስያዊያን ባህሪያቸው ይገርማል። አብዝቶ ጭምቶች ናቸው። በፍጥነት ይጓዛሉ። ተሰባስበው አያወሩም። ቢያወሩ እንኳ ሳቅ፣ ሁካታ፣ ጫጫታና ጩኸት አያሰሙም። ሽማግሌ ባለበት መድረክ እንደማያወራ የሀበሻ ልጅ እንቅስቃሴያቸው ስነ ስርዓታዊ ነው። በሞስኮ ሜትሮ ውስጥ ቡድን ጮኸ ብሎ የሚስቁና የሚጫወቱ ሰዎች ካሉ ምናልባት እኛ አፍሪካዊያን ነን።

በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ ከአናስታሲያ ጋር ስናወራ (በኢትዮጵያ አየር መንገድ የሞስኮ ቅርንጫፍ ቢሮ ባልደረባ ናት) “እኛ ሩስያዊያን ሲያዩን ቁጡ እንመስላለን። ብዙ ደማቆች አይደለንም። ግን ከሳቅን ዕውነተኛ ሳቅ ነው የምንስቀው። አናስመስልም” ነበር ያለችው። ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ያረጋገጥኩትም ነገር ቢኖር ሩስኪዎች ከወደዱ ወደዱ ነው፤ ማስመሰል አያውቁም። ሩስኪዎች ዝምታ ብቻ ሳይሆን ሰው ላይ ትኩረት አያደርጉም። ከወጣት እስከ ሽማግሌ ጆሯቸው ላይ ማዳመጫ ሰክተው፤ ሌሎቹ ስልካቸው ሏይ አፍጥጠው ይንቀሳቀሳሉ።

የሩስያዎች የስነ ጽሁፍ እና የስነ ጥበብ አሻራ መዳበር መሰረት የሆነው የማንባብ ባህላቸው ዛሬም አልጠፋም። በትራንስፖርት ቦታዎችን ጨምሮ ሩስኪዎች መፅሐፍትና ጋዜጣ ያነባሉ። በሆቴሎች ሳይቀር እንደ ቤተ መፃሕፍት በየሕንጻ ወለሎች ኮሪደር ትልልቅ የመፅሐፍት መደርደሪያዎች ተቀምጠዋል። የሆቴል ደንበኛ የፈለገውን መፅሐፍ ወስዶ አንብቦ መመለስ ይችላል።

በጎዳናዎችና ሜትሮ ጣቢያዎች ሙዚቃ እየተጫወቱ ገንዘብ የሚሰጣቸው ሰዎች በብዛት ይታያሉ። ሰዎች ገንዘባቸውን የሚለግሱት የሙዚቃ ጥበቡን አድንቀው ወይስ ድጋፍ ጠያቂዎችን ተቸግረዋል በሚል ለልመና የሚሰጥ ይሆን የሚለውን አላረጋገጥኩም።

ሌላው የሞስኮ ቆይታዬ አይጠበቄ ክስተት የቀኑና ሌሊቱ ርዝመት ወይም የፀሐይ ሥርቀትና ግባት ሁኔታ ነው። ሰዓቱ ከኢትዮጵያ ጋር ተመሳሳይ ነው። በክረምትና በጋ ባህሪያት ግን የተገላቢጦሽ ነን። እናም ወቅቱ ክረምት መሆኑ ትልቅ አጋጣሚ ነበር። የሩስያ መለያ የሆነው አስቸጋሪ ቅዝቃዜ በበጋ ወቅት እንጂ በክረምት የለም።

በክረምት ወቅት የሞስኮ ፀሐይ የምትጨልመው ዘግይታ፣ የምትሠርቀው ደግሞ ፈጥና ነው። ሞስኮ ብርሃኗ ሰፊና ረጅም ነው። ለምሳሌ አዲስ አበባ ዶሮ በሚጮኸበት ከሌሊቱ አስር ሰዓት የሞስኮ ሰማይ የአህያ ሆድ መስሏል። አስር ሰዓት ተኩል ገዳማ የሩስያ ፀሐይ በሞስኮ ውብ ሕንጻዎች ላይ ጮራዋን ትፈነጥቃለች። ይህ ብቻ አይደለም። አዲስ አበባ ሕልም ላይ በሆነችበት፣ የአራዳ መንገዶች ኦና በሆኑበት ከምሽቱ አራት ሰዓት ላይ ሞስኮ ምሽት ዓይን መያዝ ይጀምራል። ወደ ቤት ለመግባት የሚደረግ የሞስኮ ሰላማዊ ትርምስምስ ይጀምራል። በርግጥ የሞስኮ ሱፐርማርኬቶች 24 ሰዓት ክፍት ናቸው። በክረምት የሞስኮ ፀሐይ ሌሊት ወጥታ ሌሊት ትጠልቃለች። አንዱ ግርምቴ ነው። በተለይም ከሌሊቱ አስር ሰዓት ከእንቅልፌ ስባንን መስኮት ከፍቼ ቴራስ ላይ ቁጭ ብሎ ትዕይንተ ሞስኮን መቃኘት አስደስቶኛል።


 

ሰዓት አክባሪው ‘ሜትሮ’ የስርቻው ቤተ መንግስት 

ሜትሮ ማለት በሩስያኛ ከመሬት ግርጌ (ስርቻ) ወይም ባንቧ ማለት ነው። ይሄውም ከመሬት በታች በጥልቀት ተቆፍሮ የተገነባው የከተማ ውስጥ ባቡር መጠሪያ ቃል ነው። ሜትሮ የሞስኮ ሁለንተና ነው። በዕለታዊ ኑሮ ውስጥ በስፋት የሚወሳ ቃል ነው። የሜትሮ ተዘውታሪነት በመጓጓዣነት የአንበሳውን ድርሻ መያዙ ብቻ አይደለም። መሰረተ ልማቱ የተገነባበት መንገድ ከአገልግሎት ባሻገር ለከተማዋ ቅርስና መስህብ እንደሚሆን እሙን ነው።

የሞስኮ ህዝብ ሜትሮን ከመኪናው ወይም ከከተማ ባስ ይልቅ በብዙ እጥፍ ይመርጠዋል። ምክንያቱም ሜትሮ በአማካይ 90 ሰከንዶች ልዩነት እየተጥመለመለ ይደርሳል። በመሳፈሪያ ቦታ የቆመን ተሳፋሪ በሙሉ አንዴ ጎርሶት እልም ብሎ በ90 ሰከንድ ልዩነት ሌላው ይከተላል። አገልግሎት ከጀመረ 70 ዓመታት ያስቆጠረው የሞስኮ ሜትሮ ሰዓት አክባሪና አስተማማኝ የትራንስፖርት ድርጅት ነው።

ከመሬት በታች የሚርመሰመሰው ሜትሮ አስደናቂው ነገር መስመሮችን እና መሳፈሪያ ጣቢያዎች ግንባታ ጥራትና ውበት ነው። የሜትሮ ስነ ሕንጻ ጥበብ ግሩም ነው። ሜትሮ በንጹህነቱ፣ በስነ ጥበባዊ ውበቱ፣ በአጠቃላይ ገጽታው የተነሳ ‘የስርቻው ስር የሰፊ ህዝብ ቤተ መንግስት’ ይሰኛል። ሰዓት አክባሪው የስርቻው ቤት መንግስት ያልኩትም ለዚህ ነው።

ታሪካዊ ዕውነታዎች እንደሚያስረዱት የመጀመሪያው ሜትሮ መስመር አገልግሎት ፕሮጀክቶች አንዱ ሲሆን ዲዛይኑም የወደፊት ሶቬት ሕብረትን  ፍላጎት ለማንፀባረቅ እንደሆነ ይወሳል። እንደ ክር የተጥለፈለፈው የዛሬው ሜትሮ ስራ ሲጀምር ‘ከሶኮልንኪ እስከ ፓርክ ኩልተሪ’ ጣቢያዎች የሚያካልል ቀይ መስመር ሲሆን ቀጥሎም ስሞሌንስካያ እስከ ኦክታኒ ሪያድ ባቡር ጣቢያዎች የሚሸፍን ሰማያዊ መስመር ነበር። እንደ ዕድል ሆኖ ካረፍኩበት ሆቴል እስከ ስልጠና ቦታዬ ለመድረስ ቀዩ መስመር ስለነበር የሜትሮ ጣቢያዎችን በቅጡ ለመጎብኘትና ለመደነቅ ችያለሁ። በርካቶቹ ቀደምት ጣቢያዎች ከዲዛይናቸው፣ ከታሪካቸው፣ ከቅርጻ ቅርሶች፣ ስዕላትና አጠቃላይ ስነ ውበት ሲታይ ‘የስርቻው ስር ቤተ መንግስት’ ብቻ ሳይሆን ቤተ መቅደስ የሚመስል ግርም ሞገስ አላቸው።

እያንዳንዱ ጣቢያዎች የራሳቸው ልዩ አስደማሚ መልክና ማንነት አላቸው። ሜትሮ ግንባታው ጥልቀት ምስጢር የአፈሩ ሁኔታ እንደሆነ ይነገራል። በመስመር ቁፈራው ወቅትም በርካታ የከርሰ ምድር ወንዞች ተገኝተዋል። በርግጥም እንደ ጸበል የሚፈስ ውሃ ከአንድ ጣቢያ ላይ አይቻለሁ። ሜትሮን ለመጀመሪያ ጊዜ ለተመለከተ ዓይኑን መጠራጠሩ አይቀርም። ሜትሮ ውጫዊ ውበቱ ብቻም ሳይሆን ቴክኖሎጂካል ስርዓቱ አስደናቂ ነው።

ከመካከላችን የተወሰኑት በተደጋጋሚ የመጥፋት ችግር አጋጥሟቸዋል። ምክንያቱም ሜትሮ ጣቢያዎች አንድ መውጫና መግቢያ ብቻ ሳይሆን እጅግ ውስብስብ የተሳሰሩ መንገዶችና አቅጣጫዎች አሉት። በተለይም አብዛኛው ጣቢያዎች ከሌሎች ጣቢያዎች ውስጥ ለውስጥ የተሳሰሩ በመሆኑ ነው። ይህን ለመለየት ሜትሮ ብዙ አማራጮች አሉት። ሜትሮ የተሰኘው የሞባይል አፕሊኬሸን (እንደ ጎግል ካርታ) ትልቁ መሳሪያ ነው። ከየት ተነስቶ የት መድረስ እንዳለበት ከነአጭር አማራጮች የሚናገር። በየትኛው በር መስመር መቀየር እንደሚገባ፣ መስመሩ ምን አይነት ቀለም እንዳለው ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። በየፌርማታ ጣቢያዎች ላይም አቅጣጫ ጠቋሚ አማራጮች ያሉ ሲሆን ባቡሩ ውስጥ በራሱ በዲጂታል ስክሪን አመላካች አማራጮች አሉት። በዚህ ካልሆነ ግን ሜትሮ ከተማዋን በሶስት ቀለበት ይዞራታል። እያንዳንዱ ቀለበት ከሌላው እንደ ቀለበት በሁሉም አቅጣጫ እንደ ሸረሪት ድር የተሳሰሩ ነው።

397 ኪሎሜትር ርዝመት ያለው የሞስኮ ሜትሮ በስም፣ በቁጥርና በቀለም የሚለዩ 17 የሜትሮ መስመሮች፣ 265 የሜትሮ ጣቢያዎች(ፌርሜታዎች) አሉት። ወደ ሜትሮ ለመሳፈር እስከ 126 ሜትር የሚረዝሙ (740 ደረጃዎች) አሳንሰሮች (ኢሊቨተርስ) አሉት። የሞስኮ ሜትሮ በቀን እስክ 7 ሚሊዮን ሰዎችን እንደሚያጓጉዝ መረጃዎች ያሳያሉ። በነገራችን ላይ ሞስኮን ከሌሎች ከተሞችና ጎረቤት ሀገራት ጋር የሚያስተሳስሩ ባቡር ሌሎች ናቸው። ለነዚህ ፈጣን ባቡሮች ስምንት የባቡር ጣቢያዎች ሞስኮ ውስጥ ይገኛሉ።

ሞስኮ ሜትሮ ከሌሊቱ 11፤30 እስከ ሌሊቱ 7 ሰዓት የሚያገለግል፣ በሰዓት 42 ኪሎሜትር የሚሸመጥጥ ነው። ለአንድ ጉዞ ትኬት 60 ሩብል (0 ነጥብ 6 ዶላር ገዳማ) ይከፈላል። ክፍያውን በራስ አገዝ ማሽኖች ወይም በስልክ መክፈል የሚቻል ሲሆን ለሜትሮና ለህዝብ ባስ ለሁለቱም የሚያገለግል አንድ ካርድ አለ። ያ ካርድ ያልያዘ ሰው ወደ ሜትሮ ለመግባት መሿለኪያ በሮች አይከፈቱለትም። በርግጥ ሞስኮ እንኳን ሜትሮ የትም ቦታ ገንዘብ ክፍያ በጥሬ ሳይሆን ገንዘብ በተሞላ ካርድ (ከባንክ ሂሳብ ተቆራጭ በሚያደርግ) በኩል ነው። ለሻይ ሂሳብም በካርድ መክፈል ይሻላል። ዲጂታላይዜሽን ማለት እንዲህ ነው።

መውጫ

ስለሞስኮ መተረክ ‘ዓባይን በጭልፋ’ ነው። ከተማው ጥልቅና ሰፊ ነው። ይህ የእኔ ቁንጽል ማስታወሻ ነው። አፍሪካዊያንን ያስደነቀን፣ በቁጭት ያነደደን ጉዞ ነበረን። ሞስኮ የሀገር ፍቅርና ኩራት፣ ብሔራዊ ትዕምርት ፈጠራን፣ የቴክኖሎጂና ፈጣራ ከፍታና ሚናን፣ በራስ ባህልና ታሪክ መኩራትን ታስተምራለች።

የዲጂታላይዜሽን ደረጃና የሩስያ የኢንቮርሜሽን ኮሚዩኒኬሸን ቴክኖሎጂ ምጥቀት ያስገርማል። ይህ በቢሮክራሲና በሙስና የታጠረ ኅላቀር አሰራር ላይ የተቸከለውን የአፍሪካ ሀገራትን አሰራር ለማዘመን ትልቅ የቤት ስራ የሚሰጥ ነው።

ብዝሐ-ማንነት ቀጣይነት ያለው ስልጣኔ፣ ዕድገትና ብልጽግና ለማረጋገጥ እንቅፋት አለመሆኑን አያሌ የብሔር ማንነቶችን ያቀፈችው ኢትዮጵያን መሰል በማንነት ተኮር ግጭት ሰለባ ለሆኑ ሀገራት ትልቅ ትምህርት ይሰጣል። ሀገር ዘላለማዊ ክብሯንና ሉዓላዊነቷን ለማስቀጠል በኢኮኖሚ መደርጀት፣ የጦር አቅሟን ማፈርጠም እና የሰው ሀብቷን በዕውቀትና ክህሎት ማልማት እንደሚገባት ከሩስያ በላይ ምሳሌ የለም።

ሩስያ በራስ መልክ መዘመን፣ በራስ ጥበብ መራቀቅ፣ በራስ ፈጠራ የሰው ልጅን እንከን መቅረፍ እንደሚቻል በቋንቋቸው አሳይተዋል። በዓለም አቀፍ ስነ ፅሁፍ ምህዳር ውስጥ በመልማቱ የሚታወቀውና የራሱ ፊደል ያለው ሩስያኛ ቋንቋ ከቋንቋ ዕድገት ባሻገር ከቴክኖሎጂ ጋር እንዴት የተጣጣመበት ርቀት ያስቀናል። ኢትዮጵያን መሰል የራሳቸው ፊደል ያላቸው ሀገራት ቋንቋቸውን እንዴት ማልማት እንደሚችሉ ቁምነገር የሚያስጨብጥ ይመስለኛል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም