ቀጥታ፡

በቄለም ወለጋ ዞን ከ247 ሺህ ሔክታር በላይ መሬት በመኸር እርሻ በተለያዩ ሰብሎች በዘር ተሸፍኗል

ግምቢ ፤ ሐምሌ 20/2015 (ኢዜአ)፡- በቄለም ወለጋ ዞን በ2015/2016 መኸር እርሻ ከ247 ሺህ ሔክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች በዘር መሸፈኑ ተገለጸ፡፡

የዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት  ሃላፊ  አቶ ሙለታ ዋቅጅራ እንዳሉት በዞኑ በመኸር እርሻው እስካሁኑ 247 ሺህ 35 ሔክታር መሬት ታርሶ በተለያዩ ሰብሎች በዘር ተሸፍኗል፡፡ 

በምርት ዘመኑ 140ሺህ 158 አርሶ አደሮች በልማቱ እየተሳተፉ መሆኑን ገልጸው፤ ከዚህም 7 ሚሊዮን 489 ሺህ 740 ኩንታል ምርት እንደሚገኝ ታልሞ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

ምርትና ምርታማነቱን ለማሳደግም የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ለአርሶ አደሩ እየቀረበ መሆኑን ተናግረዋል። 

በዚህ መሰረት እስካሁን 48 ሺህ 645 የተለያየ የአፈር ማዳበሪያ ቀርቦ የተሰራጨ ሲሆን ቀደም ብሎም 2 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የተፈጥሮ ማዳበሪያ በአርሶ አደሩ ተዘጋጅቶ ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዞኑ በአብዛኛው የሚመረተው ለምግብ ፍጆታ የሚሆን የሰብል ዓይነት እንደሆነ ተናግረው፤ ዘንድሮ ገበያ ተኮር ሰብሎችንም ለማምረት ትኩረት በመስጠት እየተሰራ ነው ብለዋል።      

ማሳቸውን በዘር ከሸፈኑት የዞኑ አርሶ አደሮች መካከል የዳሌ ሳዲ ወረዳ ነዋሪው አቶ ለሜሳ ዱላ አንድ ሔክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች በዘር ሸፍነዋል።

የሚያሰፈልጋቸውን ግብዓቶች በግዜ እንዳገኙና አሁን ያለው የአየር ሁኔታም ለመኸር አዝመራዉ ምቹ እንደሆነም አብራርተዋል፡፡

አክለውም የእርሻ መሬታቸውንም በኩታ ገጠም መዝራታቸውን ተናግረው፤ በዚህም ጥሩ ምርት እንደሚጠብቁ ነው የተናገሩት፡፡

የጊዳሚ ወረዳ ነዋሪው አርሶ አደር አብዳታ ያደታ በበኩላቸው ለመኸር አዝመራው  በቂ ዝግጅት በማድረጋቸው ያላቸውን ግማሽ ሔክታር መሬት በዘር መሸፈናቸውን ተናግረዋል፡፡

የዘንድሮ ዝናብና አየር ሁኔታ ለእርሻው አመቺ እንደሆነም አክለው ተናግረዋል፡፡

አርሶ አደሩ ዓምና በኩታ ገጠም በመዝራታቸው ያገኙት ምርት ጥሩ በመሆኑ ዘንድሮም  መሬታቸውን በኩታ ገጠም እንዳረሱ ነው የገለጹት።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም