ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በሴካፋ ከ18 ዓመት በታች የሴቶች እግር ኳስ ውድድር ሁለተኛ ጨዋታዋን ከታንዛንያ ጋር ታደርጋለች

አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 20/2015 (ኢዜአ) :- ኢትዮጵያ በምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ የእግር ኳስ ማህበራት ምክር ቤት (ሴካፋ) ከ18 ዓመት በታች የሴቶች እግር ኳስ ውድድር ሁለተኛ ጨዋታዋን ዛሬ ከታንዛንያ ጋር ታደርጋለች።

ውድድሩ ዛሬ ሶስተኛ ቀኑን የያዘ ሲሆን ታንዛንያ፣ ኢትዮጵያ፣ ዩጋንዳ፣ ብሩንዲ እና ዛንዚባር እየተሳተፉበት ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ከ18 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከውድድሩ አዘጋጅ ታንዛንያ ጋር ከምሽቱ 12 ሰአት ላይ በቻማዚ ስታዲየም ጨዋታውን ያደርጋል።


 

ኢትዮጵያ በመጀመሪያ ጨዋታዋ በዩጋንዳ 1 ለ 0 የተሸነፈች ሲሆን ታንዛንያ ብሩንዲን 3 ለ 0 ማሸነፏ ይታወሳል።

ብሔራዊ ቡድኑ ከታንዛኒያ ጋር ለሚያደርገው ጨዋታ ትናንት በኡሁሩ ስታዲየም ልምምዱን አከናውኗል።

በሌላኛው የውድድሩ መርሐ-ግብር ዩጋንዳ እና ዛንዚባር ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ለመጀመሪያ ጊዜ በሚካሄደው የሴካፋ ከ18 ዓመት በታች የእግር ኳስ ውድድር ሰባት አገራት ውድድራቸውን በሁለት ምድብ ተከፍለው እንዲያደርጉ መርሐ-ግብር ወጥቶላቸው ነበር።


 

ይሁንና ኬንያ እና ሩዋንዳ አብዛኞቹ ተጫዋቾቻቸው ብሔራዊ ፈተና የሚፈተኑ በመሆናቸው ምክንያት ከውድድሩ ራሳቸውን እንዳገለሉ መግለጻቸው ይታወሳል።

በዚህም ምክንያት የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ የእግር ኳስ ማህበራት ምክር ቤት የውድድሩን ፎርማት በመቀየር አምስቱ አገራት እርስ በእርሳቸው የሚጫወቱበትን አማራጭ (round robin format) ለመጠቀም ተገዷል።

እርስ በእርስ ጨዋታው የተሻለ ውጤት ያስመዘገበ አገር የውድድሩ አሸናፊ ሲሆን ሌሎቹ አገራት እንደ ውጤታቸው ደረጃቸውን ያገኛሉ።

ውድድሩ እስከ ነሐሴ 1/2015 ድረስ እንደሚቆይም ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም