መንግስት የፈተና ኩረጃን ለማስቀረት የወሰደው እርምጃ በራስ የመተማመን አቅማችንን አጎልብቷል- ተፈታኝ ተማሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት የፈተና ኩረጃን ለማስቀረት የወሰደው እርምጃ በራስ የመተማመን አቅማችንን አጎልብቷል- ተፈታኝ ተማሪዎች
ጎንደር ፤ ሐምሌ 20/2015 (ኢዜአ)፡- ''መንግስት የፈተና ኩረጃን ለማስቀረት የወሰደው ጠንካራ እርምጃ በራስ የመተማመን አቅማችን የገነባ ነው'' ሲሉ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ 12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና የወሰዱ ተማሪዎች ተናገሩ፡፡
በዩኒቨርሲቲው ከተፈተኑት መካከል ተማሪ አቤል ብርሃን እንዳለው ወደ ፈተናው በራስ የመተማመን ስሜት በመግባቱ የዛሬውን ፈተና በጥሩ ሁኔታ ተፈትኗል።
የፈተና ሂደቱ ፍጹም ሰላማዊና ከኩረጃም ነጻ በመሆኑ ጠንክሮ ያጠና ተፈታኝ የልፋቱን ዋጋ እንደሚያገኝ እርግጠኛ ሆኖ ፈተናውን መውሰዱንም ተናግሯል።
ተማሪ ማህሌት አስማረ በበኩሏ ኩረጃ የደካማ ተማሪዎች መገለጫ በመሆኑ መንግስት ኩረጃን ለማስቀረት የወሰደው እርምጃ ሁሉም ተማሪ የልፋቱን ውጤት እንዲያገኝ ምቹ ሁኔታ የፈጠረ ነው ብላለች።
"ከእዚህ በኋላ ኩረጃን ተማምኖ ለፈተና የሚመጣ ተማሪ እድሉ የተዘጋ ነው" ያለችው ተማሪዋ፣ የዛሬን ፈተና በአጥጋቢ ሁኔታ መስራቷን ተናግራለች።
ከዚህ ቀደም የፈተና ስርቆትና ኩረጃ ስለነበር የጎበዝ ተማሪዎች ልፋትና ድካም ከንቱ ይቀር ነበር ያስታወሰችው ደግሞ ተማሪ ሙሉ ገበያው ነች።
"ለፈተናው ሁሉም የአቅሙንና የችሎታውን ተዘጋጅቶ መጥቷል፤ እኔም በልፋቴ ልክ ወደ ዩኒቨርሲቲ የመግባት ህልሜን እንደማሳካ እርግጠና ነኝ'' ብላለች።
መንግስት ፈተናውን በዩኒቨርሲቲዎች በጥንቃቄ እንዲሰጥ ማድረጉ እሷን ጨምሮ ለፈተናው ተገቢ ዝግጅት ላደረገ ተማሪ በራስ የመተማመን አቅምን ማሳደጉን ተናግራለች።
ዛሬ በተጀመረው ሀገር አቀፍ ፈተና በጎንደር ዩኒቨርሲቲ 11ሺህ 348 የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች ለፈተናው መቀመጣቸውን የገለጹት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር አስራት አጸደወይን ናቸው።
የትምህርት ጥራት ከሚረጋገጥባቸው መንገዶች አንዱ የፈተና ኩረጃን ከመሰረቱ ማስቀረት እንደሆነ ጠቅሰው፣ ዩኒቨርሲቲው በሀገራዊ ፈተናው ይህን ሀገራዊ ሃላፊነት እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል።
ለፈተናው ስኬታማነት አስቀድሞ በተደረገ በቂ ዝግጅት የዛሬው የፈተና ሂደት ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መንገድ መጠናቀቁን አስረድተዋል።
ዩኒቨርሲቲው በማህበራዊና በተፈጥሮ ሳይንስ 40 ሺህ 340 የ12ኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎችን በሁለት ዙር እንደሚያስፈትን ለማወቅ ተችሏል።