ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ እና ማላዊ ለረጅም ጊዜ የቆየውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገለጹ

አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 19/2015 (ኢዜአ) ፡- ኢትዮጵያ እና ማላዊ ለረጅም ጊዜ የቆየውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ለማጠከር ቁርጠኛ መሆናቸውን አስታወቁ።

“የአፍሪካን የኢኮኖሚ እድገት ማፋጠን፤ ወጣቶችን በትምህርት እና ክህሎት በማብቃት ምርታማነታቸውን ማሳደግ” በሚል መሪ ሃሳብ በታንዛንያ ዳሬሰላም ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የአፍሪካ የሰው ሀብት ልማት የመሪዎች ጉባኤ ዛሬ ተጠናቋል።

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የተመራ ከፍተኛ የኢትዮጵያ ልዑክ በጉባኤው ላይ ተሳትፏል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከጉባኤው ጎን ለጎን ከማላዊ ፕሬዚዳንት ዶክተር ላዛሩስ ቼክዌራ ጋር ሁለቱ አገራት በሁለትዮሽ፣ አህጉራዊ እና የባለ ብዙ ወገን ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ትብብር ማጠናከር በሚችሉባቸው ሁኔታዎች ላይ ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም አገራቱ ያላቸውን ታሪካዊ እና የባለ ብዙ ወገን የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ ለማሳደግ ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት አፈጻጻም ያለበትን ደረጃ አስመልክተው ለፕሬዚዳንቱ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ማላዊ የኢትዮጵያን ሰላምን የማጽናት ሂደት እንድትደግፍ ጥሪ አቅርበዋል።

ፕሬዚዳንት ቼክዌራ የሰላም ስምምነቱን በጣም ወሳኝ ያሉት ሲሆን፤ በሱዳን ያለውን ግጭት በመሸሽ ወደ ኢትዮጵያ ለመጡ የማላዊ ዜጎች ኢትዮጵያ ያደረገችውን አቀባበል አድንቀዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከአፍሪካ የሰው ኃይል ልማት የመሪዎች ጉባኤ መጠናቀቅ በኋላ ከታንዛንያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን(TBC) ጋር የኢትዮጵያ እና የማላዊ የሁለትዮሽ ግንኙነት ላይ ያተኮረ ቆይታ አድርገዋል።

በቆይታቸውም ሁለቱ አገራት የኢትዮ-ማላዊ ቋሚ የጋራ ትብብር ኮሚሽን ስብሰባ ለማድረግ መስማማታቸውን ገልጸዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከጉባኤው ጎን ለጎን ከሴራሊዮን ፕሬዚዳንት ዶክተር ጁሊየስ ማዳ ቢዮ ጋር የአገራቱ የሁለትዮሽ፣ አህጉራዊ እና የባለ ብዙ ወገን ትብብርን ማጠናከር በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ መወያየታቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም