ቀጥታ፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከሴራሊዮን ፕሬዝዳንት ዶክተር ጁሊየስ ማዳ ቢዮ ጋር ተወያዩ 

አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 19/2015 (ኢዜአ)፡- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከሴራሊዮን ፕሬዝዳንት ዶክተር ጁሊየስ ማዳ ቢዮ ጋር ውይይት አድርገዋል።

ለሁለት ቀናት “የአፍሪካን የኢኮኖሚ እድገት ማፋጠን፤ ወጣቶችን በትምህርት እና ክህሎት በማብቃት ምርታማነታቸውን ማሳደግ” በሚል መሪ ሃሳብ በታንዛንያ ዳሬ ሰላም ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የአፍሪካ የሰው ሀብት ልማት የመሪዎች ጉባኤ ዛሬ ተጠናቋል።

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የተመራ ከፍተኛ ልዑክ በጉባኤው ላይ ተሳትፏል።

አቶ ደመቀ ከጉባኤው ጎን ለጎን ከሴራሊዮን ፕሬዝዳንት ዶክተር ጁሊየስ ማዳ ቢዮ ጋር የሁለቱ አገራት የጋራ ፍላጎቶች በሆኑ በሁለትዮሽ፣አህጉራዊ እና የባለ ብዙ ወገን ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገዋል።
 

ሁለቱ ወገኖች የአገራቱ መንግስታት በተለያዩ መስኮች እያከናወኗቸው ባሏቸው ስራዎች ያስመዘገቧቸውን ስኬቶች አስመልክቶ ሀሳብ ተለዋውጠዋል።

አቶ ደመቀ የኢትዮጵያ መንግስት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር፣የሌማት ትሩፋት፣የስንዴ ምርት እና “ትምህርት ለትውልድ” ንቅናቄ አስመልክቶ ለፕሬዝዳንቱ ገለጻ አድርገዋል።

ኢትዮጵያ ከሴራሊዮን ጋር ያላትን የሁለትዮሽ፣ አህጉራዊ እና የባለብዙ ወገን ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር እንደምትፈልግ አመልክተዋል።  

አቶ ደመቀ ሴራሊዮን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል ሆና በመመረጧ ለአገሪቷ ፕሬዝዳንት የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የሴራሊዮን ፕሬዝዳንት ዶክተር ጁሊየስ ማዳ ቢዮ ከሰው ኃይል ልማት ጋር የተቆራኘውን የምግብ ዋስትና፣ግብርና እና ጤና ስራዎች አስመልክቶ የአገራቸውን ተሞክሮ ለአቶ ደመቀ አጋርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም