ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር  በመተማ ዮሐንስ ከተማ ለሚገኙ ስደተኞች ከ14 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ

መተማ ፤ ሐምሌ 19/2015 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በሱዳን ግጭት ምክንያት ተፈናቅለው በመተማ ዮሐንስ ከተማ ለሚገኙ ስደተኞች ከ14 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።

በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የሰሜን ጎንደር ዞን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አታለል ታረቀኝ እንዳሉት ድጋፉ ብርድ ልብስና አንሶላ፣ የንፅህና መጠበቂያ፣ መጠለያ ሸራ፣ የማብሰያ ቁሳቁሶች፣ የውሃ ባልዲና የመኝታ ምንጣፍ ያካተተ ነው።

ድጋፉም ከሱዳን ተፈናቅለው በመተማ ዮሃንስ ከተማ ለተጠለሉ ኢትዮጵያዊ፣ ኤርትራዊና ሱዳናዊ ዜጎች የሚውል መሆኑን ጠቅሰው፤ ድጋፉም ከ4 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሚያገለግል መሆኑን ገልጸዋል።

የቀይ መስቀል ማህበር ከሌሎች ድጋፍ ሰጭ ተቋማት ጋር በመተባበር ከዚህ በፊትም ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ምግብ ነክና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችን ድጋፍ ማድረጉን አስተባባሪው ተናግረዋል።

ዛሬ የተደረገው ድጋፍ የመኝታና የመጠለያ ችግራቸውን በመጠኑም ቢሆን የሚያቃልል መሆኑን አብራርተዋል።

ድጋፍ ከተደረገላቸው መካከል ወይዘሮ ሰዓዳ አብዱልቃሲም እንዳሉት ሱዳን ባለው ግጭት ተፈናቅለው ወደ መተማ ዮሃንስ ከመጡ ሁለት ወራት አሳልፈዋል።

አምስት የቤተሰብ አባላት እንዳሏቸው ጠቅሰው፤ አሁን የተደረገላቸው ድጋፍ የመጠለያና የመኝታ ችግራቸውን የሚቀርፍ መሆኑን ተናግረዋል።

አቶ ቃለአብ ገብረህይወት በበኩላቸው ከነበሩበት ካርቱም ከተማ ግጭቱን ሸሽተው ከመጡ ከሁለት ወራት በላይ ሆኗቸዋል።

 ''አሁን የተደረገው ድጋፍ የነበረውን ችግር የሚቀርፍ ነው'' ሲሉ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያውያን እና አለም ዓቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች እያደረጉት ላለው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበው፤ ቀጣይም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም