ዳያስፖራው በአገራዊ ጉዳይ ላይ እያደረገ ያለው ተሳትፎ ይበልጥ መጠናከር አለበት- አምባሳደር ባጫ ደበሌ - ኢዜአ አማርኛ
ዳያስፖራው በአገራዊ ጉዳይ ላይ እያደረገ ያለው ተሳትፎ ይበልጥ መጠናከር አለበት- አምባሳደር ባጫ ደበሌ
አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 19/2015 (ኢዜአ) ፡- ዳያስፖራው በአገራዊ ጉዳይ ላይ እያደረገው ያለው ሁለንተናዊ ተሳትፎ አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ባጫ ደበሌ ገለጹ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎትን ያካተተው የልዑካን ቡድን በኬንያ ከሚገኙ ከተለያዩ የኮምዩኒቲ ማህበራት አደረጃጀት ተወካዮች፣ ባለሃብቶች፣ የሙያ ማህበራትና የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ መሪዎች ጋር በናይሮቢ ውይይት አካሄዷል።
በውይይቱ በሀገሪቱ ወቅታዊ ጉዳይ፣ ዳያስፖራው በአገሩ ጉዳይ እያደረገ ያለውን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ በመንግስት በተመቻቹ ማዕቀፎች እንዲሁም ዳያስፖራው የልማት ተሳትፎውን ማጎልበት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ገለጻ ቀርቧል፡፡
በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ባጫ ደበሌ ፈተናዎችን ለመሻገር የመንግስት አካላትና ዳያስፖራው በትብብር መስራታቸውን አጠናክረው መቀጠል አለባቸው ብለዋል።
የዳያስፖራ አደረጃጀቶች ከምንጊዜውም በላይ መጠናከርና ጥምረት መስርተው የመንቀሳቀሳቸውን አስፈላጊነት ያነሱት አምባሳደሩ የአደረጃጀቶቹ ተሳትፎና ትስስር ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚሰራም ገልጸዋል።
በኬንያ የሚኖሩ የዳያስፖራ አባላት ለአገራዊ ጥሪ ለሚሰጡት ፈጣን ምላሽ አመስግነው እያደረጉ ያለውን ሁለንተናዊ ተሳትፎ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የኢትዮጵያን ልማት ለማገዝ እያደረጓቸው ያሉ እንቅስቃሴዎችን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
ከውይይቱ በተጨማሪ የልዑካን ቡድኑ የዳያስፖራ ኢንቨስትመንቶችን ጎብኝቷል።