ቀጥታ፡

ለብልሹ አሠራር የተጋለጡ መንግሥታዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ሊደረግ ይገባል - የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም

አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 19/2015 (ኢዜአ)፡- ለብልሹ አሠራር የተጋለጡ መንግሥታዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ሊደረግ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም አሳሰበ፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በአዋጅ ቁጥር 1142/2011 እና የመረጃ ነፃነት አዋጅ ቁጥር 590/2000 መሠረት አስፈጻሚ አካላት በዜጎች ላይ የሚያደርሱትን አስተዳደራዊ በደሎች በመመርመር የመፍትሔ ሃሳብ የማቅረብ ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡

ተቋሙ በ2015 በጀት ዓመት በ52 ጉዳዮች 164 ተቋማት ላይ ቁጥጥር ለማድረግ አቅዶ በ47 ጉዳዮች 164 ተቋማት ላይ ቁጥጥር ማድረጉን በዓመታዊ ሪፖርቱ ላይ አመላክቷል።

የመንግሥት ግዥ ሥርዓት ግልጸኝነትና አሳታፊነት፣ የካሳ ክፍያና ምትክ መሬት አሰጣጥ፣ የግብርና ግብዓት ተጠቃሚነት፣ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦትና መልሶ ማቋቋም፣ የቅድመ ማስጠንቀቅ ሥርዓት፣ አገልግሎት አሰጣጥና አስተዳደራዊ በደሎች በዋናነት ቁጥጥር የተደረገባቸው ናቸው።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በቀረቡ 7 ሺህ 416 አቤቱታዎች ውስጥ 277 ሺህ 698 ሰዎች ሲኖሩ 2 ሺህ 235 አቤቱታዎች ከሥራ ጋር የተገናኙ፣ 1 ሺህ 772 በአገልግሎት እጦት እንዲሁም 1 ሺህ 588 አቤቱታዎች ደግሞ የይዞታ ጉዳዮች መሆናቸው ተገልጿል፡፡

ከቀረቡት አቤቱታዎች በ35 መዝገቦች የተካተቱ 1 ሺህ 332 ሠራተኞችን ወደ ሥራ መመለስ፣ የደረጃ እድገት እንዲያገኙና እስከ አሥር ወር ያልተከፈለ ደመወዝ እንዲከፈላቸው ማድረግ ተችሏል።

በበጀት ዓመቱ በ24 መዝገቦች ላይ የወንጀል ክስ ተመስርቶ ዘጠኙ እልባት ሲያገኙ 15ቱ በሂደት ላይ መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን፤ ከቀረቡ የመፍትሔ ሃሳቦች 61 በመቶ የሚሆኑት ገቢራዊ ተደርገዋል ተብሏል፡፡

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ዋና ዕንባ ጠባቂ ዶክተር እንዳለ ኃይሌ፤ የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት የፈጸሟቸውን አስተዳደራዊ በደሎች በመመርመር ለሚቀርቡ የመፍትሔ ሀሳቦች የሚሰጠው ምላሽ እየተሻሻለ መሆኑን ያስረዳሉ።

ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በምናቀርበው ልዩ ሪፖርት መሠረትም አስፈጻሚ አካላት የተሰጣቸውን የመፍትሔ ሐሳብ እንዲተገብሩ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በልዩ ሪፖርት ለምክር ቤት በማቅረብ፣ በመገናኛ ብዙኃን በማጋለጥ፣ እንዲሁም በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራ እያከናወነ ቢሆንም፤ የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ በብዙ መሻሻል ይኖርበታል ብለዋል፡፡

በአንዳንድ ከተሞች የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ "በጉቦ ብቻ ሆኗል" የሚሉት ዶክተር እንዳለ፤ በተለይም የመሬትና መሬት ነክ ጉዳዮች፣ የተሽከርካሪ ታርጋ የማውጣት ሂደት ችግሩ የከፋ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በአንዳንድ ከተሞች ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎትን በጊዜና በጥራት የመስጠት ችግር ከመኖሩ ባለፈ የጉቦ ክፍያ መቀበል ግዴታ በሚመሰል መልኩ ቀጥሏል ብለዋል።

የሥራ ቅጥር፣ የፓስፖርትና የመኪና ታርጋ ማውጣት፣ የመሬትና መሬት ነክ አገልግሎቶች በብዛት በዕውቅና፣ በምልጃና በገንዘብ መሆኑን አረጋግጠናል ብለዋል፡፡

በአንዳንድ ከተሞች ዜጎች በአገልገሎት አሰጣጡ እየተማረሩና ከፍተኛ እንግልት እየደረሰባቸው መሆኑን ጠቅሰው ለብልሹ አሠራር የተጋለጡ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ሊደረግ ይገባል ብለዋል።

የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችም በተቋማቸው የአገልግሎት አሰጣጡን በመፈተሽ አፋጣኝ የማስተካከያ እርምጃና የአሰራር ማሻሻያ ማድረግ አለባቸው ነው ያሉት። 

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም