በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር የጀመርነው የዶሮና የወተት ላም እርባታ ተጠቃሚ አድርጎናል - የጂንካ ከተማ ነዋሪዎች

ጂንካ፤ሐምሌ 18/2015(ኢዜአ)፡- በጂንካ ከተማ በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር የጀመሩት የዶሮና የወተት ላም እርባታ ከቤት ውስጥ ፍጆታ አልፎ  ቋሚ የገቢ ምንጭ እንደሆነላቸው የመርሃ ግብሩ ተሳታፊዎች ተናገሩ።

የደቡብ ኦሞ ሴቶች ሊግ አባላት፣  ከየወረዳው የተውጣጡ ሞዴል ሴት አርሶና አርብቶ አደሮች እንዲሁም የዞኑ ከፍተኛ አመራሮች በከተማዋ በመርሐ ግብሩ እየተካሄዱ ያሉትን ተግባራት ዛሬ ጎብኝተዋል።

ከመርሐ ግብሩ ተጠቃሚዎች መካከል በከተማዋ ደምወዝ ሰፈር በዶሮ እርባታ ሥራ የተሰማሩት ወይዘሮ ይፍቱስራ ብዙነህ በጥቂት ዶሮዎች የጀመሩት ሥራ ውጤታማ እያደረጋቸው መሆኑን ተናግረዋል።


 

በአሁኑ ወቅት 200 ዶሮዎችን በማርባት ከቤት ፍጆታቸው አልፎ ቋሚ የገቢ ምንጭ እንደሆናቸው ገልጸው፣ በተጨማሪም የ45 ቀን ጫጩት በማርባት ለገበያ በማቅረብ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

"የዶሮ እርባታውን አዋጭነት በመመልከት ቁጥራቸውን 12 ሺህ ለማድረስና ስራውን ለማስፋፋት እየተዘጋጀሁ ነው። ከእርባታ ባገኘሁት ገቢም የመኖሪያ ቤት መስራት ችያለሁ" ብለዋል።

የግብርና ባለሙያዎች ለሚያረቧቸው ዶሮዎች ክትባትና ህክምና እንዲሁም የክህሎት ስልጠና በመስጠት የሚያደርጉላቸው ድጋፍ ለስኬት እንዳበቃቸው ወይዘሮ ይፍቱስራ ተናግረዋል።

በከተማዋ የአርክሻ ቀበሌ ነዋሪና በወተት ላሞች እርባታ ስራ ላይ የተሰማሩት መምህርት መርከብ ጌታሁን እንዳሉት ከመደበኛ ሥራቸው በተጓዳኝ በግቢያቸው በሁለት ድቅል የወተት ላሞች የጀመሩት ሥራ ውጤታማ አድርጓቸዋል።

''በትርፍ ጊዜዬ ከብቶችን በማርባትና እነሱን እየተንከባከብኩ ኑሮዬን ማቅለል ችያለሁ'' ሲሉም ተናግረዋል።


 

በአሁኑ ወቅት የሚያረቧቸው የወተት ላሞች ቁጥር 10 መድረሱን የገለጹት መምህርት መርከብ፣ ከአንድ ላም በቀን ከ15 እስከ 20 ሊትር ወተት እንደሚያገኙ አስረድተዋል። 

ወተቱንም ለአካባቢው ማህበረሰብ በተመጣጣኝ ዋጋ እንደሚሸጡ ገልጸው ለሶስት ሰራተኞችም ቋሚ የስራ እድል መፍጠር እንደቻሉም ተናግረዋል።

በተመሳሳይ በጂንካ ከተማ መሀል አራዳ ቀበሌ በወተት ላም እርባታ ላይ የተሰማሩት ወይዘሮ ምንዳዬ አልታዬና ባለቤታቸው አቶ ገዛኸኝ አዲሱ ከመርሐ ግብሩ ተጠቃሚ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

"ለልጆቻችን ወተት ለማግኘት በሁለት ላሞች የጀመርነው እርባታ በአሁኑ ሰዓት 12 ደርሰዋል" ብለዋል።

ለአራት ሰራተኞች ቋሚ የስራ እድል መፍጠራቸውንም በመጠቆም።

''የቤት ፍጆታችንን ለማሟላት የጀመርነው ስራ አድጎ ለአካባቢው ማህበረሰብ ወትት፣ አይብና ቅቤ በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ እንድንችል አድርጎናል'' ነው ያሉት።

በልምድ ልውውጡና በምልከታው ላይ የተገኙት የኛንጋቶም ወረዳ አርብቶ አደር ሀና ሬማን በጉብኝቱ ባዩት ነገር መደሰታቸውንና በቂ እውቀት መቅሰማቸውን ገልጸው፣ ይህንንም ለመተግበር እንዳቀዱ ተናግረዋል።

በብልጽግና ፓርቲ የደቡብ ኦሞ ዞን የሴቶች ሊግ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ሁሉአገር አልቴ የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር ነዋሪዎችን ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

በዞኑ ከ51 ሺህ በላይ ሴቶች በመርሐ ግብሩ በዶሮና የወተት ላም እርባታ በመሳተፍ ተጠቃሚ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

ኅብረተሰቡ በየአካባቢው ያሉትን ጸጋዎች በመጠቀም እያካሄደ ያለው መርሐ ግብር የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ አልፎ ቋሚ የገቢ ምንጭ በመሆን ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም