በኢትዮጵያ የንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፉን ይበልጥ የተቀላጠፈና ምቹ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት የግሉ ዘርፍ የነቃ ተሳትፎ ሊኖረው ይገባል- የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፉን ይበልጥ የተቀላጠፈና ምቹ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት የግሉ ዘርፍ የነቃ ተሳትፎ ሊኖረው ይገባል- የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር
አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 18/2015 (ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ የንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፉን ይበልጥ የተቀላጠፈና ምቹ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት የግሉ ዘርፍ የነቃ ተሳትፎ ሊኖረው እንደሚገባ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ገለጸ።
የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርና ከፓን አፍሪካ ንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት ጋር በመሆን የምክክር መድረክ አዘጋጅቷል።
ከዛሬ ጀምሮ ለሁለት ቀናት የሚካሄደው መድረክ የግብርና ማቀነባበር፣ ቱሪዝም ዲጂታል ግብይት/ዲጂታል ማርኬቲንግ/ ላይ ትኩረት ያደረገ ነው።
በመድረኩ የግልና የመንግስት ተቋማት ተወካዮች በመሳተፍ ላይ ሲሆኑ የግሉን ዘርፍ በመሰረታዊነት የሚያጋጥሙ ችግሮችና መፍትሄዎች ላይ ትኩረት አድርጓል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ ተሻለ በልሁ፤ የግሉን ዘርፍ ችግሮች ለይቶ መፍትሄ ለማበጀት ሐምሌ 1 ቀን 2002 ዓ.ም የጋራ መድረክ መመስረቱን አስታውሰዋል።
በንግድ ሥራ ላይ የሚሳተፈው የግሉ ዘርፍ ፈጣንና ምቹ አገልግሎት እንዲያገኝ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው በዘርፉ ዙሪያ የሚያጋጥሙ ማነቆዎች እንዲስተካከሉ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ሊጠናከር ይገባል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ኢንጂነር መላኩ እዘዘው፤ የግብርና ማቀነባበር ዘርፍ ለስራ ዕድል ፈጠራ፣ ለአገራዊ ምርት እድገት ማደግ ወሳኝ ሚና ያለው ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች በሚፈለገው ደረጃ ላይ አልደረሰም ብለዋል።
የጥሬ ዕቃ በሚፈለገው መጠን አለመገኘቱ፣ ማቀነባበር እና ምርት አስተሻሸግ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች፣ የገበያ አማራጮች አለመስፋት፣ የመሰረተ ልማት አለመሟላትና ፋይናንስ እጥረቶች ጎልተው ከሚጠቀሱ ችግሮች መካከል መሆናቸውንም ተናግረዋል።
የግብርና ሚኒስትር ደኤታ ዶክተር ሶፊያ ካሳ፤ በሰጡት ማብራሪያ በግብርና ምርት ማቀነባበር ላይ የሚስተዋሉ የጥሬ እቃ የአቅርቦት ችግሮችን ለመፍታት ምርታማነትን ማሳደግ ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
የግብርና ግብአቶች ላይ ድጎማ ማድረግ፣ አርሶ አደሮች በኩታ ገጠም እንዲያርሱ ማድረግና ዘመናዊ የግብርና መሳሪያዎችን በማቅረብ በኩል ሁሉን አቀፍ ጥረቶች በመደረግ ላይ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
የግሉ ዘርፍ ለግብርና ማቀነባበር የሚያስፈልጉ ጥሬ ዕቃዎችን በምን ያህል መጠን፣ በምን ያህል የጥራት ደረጃ እንደሚፈልግ አስቀድሞ ማሳወቅ ላይ ያሉ ውስንነቶችን በቅንጅት መፍታት ይጠይቃል ብለዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ደኤታ ታረቀኝ ቡሉልታ፤ የግል ባለሃብቱን የሚያሳትፉ 17 የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ወደ ሥራ ለማስገባት ርብርብ እየተደረገ ሲሆን የቡሬ፣ ቡልቡላ እና ይርጋለም የግብርና ማቀነባበሪያ ፓርኮች ወደ ሥራ መግባታቸውን ገልጸዋል።
ከምርት አስተሻሸግ፣ ከወጪና ገቢ ንግድና የጥሬ እቃ አቅርቦት ጋር የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።