ቀጥታ፡

ከካርበን ሽያጭ የሚገኘውን ገቢ ከፍ ማድረግ የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - የኢትዮጵያ የደን ልማት

አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 18/2015 (ኢዜአ)፡- በአገር አቀፍ ደረጃ ከካርበን ሽያጭ የሚገኘውን ገቢ ከፍ ማድረግ የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የኢትዮጵያ የደን ልማት ገለጸ።

የካርበን ሽያጭ ማለት የደን መጨፍጨፍን በመከላከል ለተጠበቀው ደን ወይም አዳዲስ ችግኞችን በመትከል የካርበን ልቀትን በመቀነስ ደን ላበረከተው አስተዋጽዖ የሚከፈል ክፍያ ነው።

ክፍያው ደን ለአካባቢውና ለአየር ንብረት ሚዛናዊነት ጥበቃ በያዘው የካርበን መጠን እንደየ ብዛቱና መጠኑ በቶን ተለክቶ ያደጉ አገራት በማደግ ላይ ላሉ አገራት የሚከፍሉት የገንዘብ ክፍያ ነው።

ኢትዮጵያ እስካሁን ከካርበን ሽያጭ ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘቷን በኢትዮጵያ የደን ልማት የብሔራዊ የሬድ ፕላስ አስተባባሪ ዶክተር ይተብቱ ሞገስ ለኢዜአ ተናግረዋል።

አሁን ላይ ኢትዮጵያ ከዚህ ዘርፍ የምታገኘውን ገቢ ከፍ ለማድረግና በተለይም በአገር አቀፍ ደረጃ ወጥ በሆነ መልኩ የካርበን ሽያጭ ለማከናወን እየሰራች መሆኑን ገልፀዋል።

የካርበን ሽያጭ ለመፈጸም በርካታ መስፈርቶችና ረዥም ሂደት የሚጠይቅ መሆኑን ጠቁመው፤ ከእነዚህ መካከል መረጃዎች በዲጂታል መልኩ በጂ ፒ ኤስ ተመዝግቦ መቅረብ ይኖርበታል ብለዋል።


 

በተለይም ደኑ ምን ያህል ሄክታር መሬት እንደሚሸፍን፣ የደኑ ሁኔታ፣ የካርበን መያዝ አቅሙና ሌሎች አስፈላጊ መረጃዎች ተጠናቅረው መቅረብ እንዳለባቸው ነው ያነሱት።

ከዚህ አንጻር በተለይም ከሁለት ዓመታት በኋላ የካርበን ሽያጩን መጀመር የሚያስችሉ ዝግጅቶች እየተከናወኑ መሆኑን ነው ዶክተር ይተብቱ የተናገሩት።

በአገሪቱ የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር አሁን ላይ ከ17 በመቶ በላይ የደረሰውን የአገሪቱን የደን ሽፋን በመጨመር የካርበን ሽያጭን ከፍ ለማድረግ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

ይሁንና የካርበን ሽያጭ ለማከናወን የሚተከለው ችግኝ ደን መሆን እንዳለበት አሳስበው፤ ደን ማለት በአንድ ሄክታር መሬት ቢያንስ 1 ሺህ ዛፍ ሊይዝ ይገባል ብለዋል።

በመሆኑም በመርሃ-ግብሩ በተቀናጀና በባለሙያዎች በመመራት ለደን የሚሆኑ ችግኞችን በአንድ ቦታ በመትከል የአገሪቱን የደን ልማት ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

አገሪቱ ከካርበን ሽያጭ የምታገኘውን ገቢ ለማሳደግ በአገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብርን ይበልጥ ማጠናከር ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም