መገናኛ ብዙኃን ዘመኑ በሚጠይቀው ልክ መረጃ የማሰራጨት ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል- ዶክተር አብዱልአዚዝ ዲኖ - ኢዜአ አማርኛ
መገናኛ ብዙኃን ዘመኑ በሚጠይቀው ልክ መረጃ የማሰራጨት ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል- ዶክተር አብዱልአዚዝ ዲኖ
አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 18/2015 (ኢዜአ)፡- መገናኛ ብዙኃን ራሳቸውን በቴክኖሎጂ እና በሰው ኃይል በማጠናከር ዘመኑ በሚጠይቀው ልክ መረጃን የማሰራጨት ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል ሲሉ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ትምህርት ቤት ኃላፊ ዶክተር አብዱልአዚዝ ዲኖ ገለጹ፡፡
የዲጂታል ሚዲያው ፈጣን መረጃን ለኅብረተሰቡ ለማዳረስ ይዞት የመጣውን ዕድልና ተግዳሮት በመለየት የጋራ አቋም ይዞ ለመሥራት ያለመ ስልጠና ለተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች እየተሰጠ ነው።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ትምህርት ቤት ኃላፊ ዶክተር አብዱልአዚዝ ዲኖ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በአሁኑ ወቅት የመገናኛ ብዙኃን አካሄድ በፍጥነት እየተለዋወጠ መጥቷል፡፡
በተለይ የማኅበራዊ ሚዲያው መበራከት ዜጎች ትክክለኛውን መረጃ ከሐሰተኛው ለመለየት አዳጋች እንዲሆንባቸው እያደረገ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም ''መገናኛ ብዙኃን የማኅበራዊ ሚዲያውን ጫና ለመቋቋም አሠራራቸውን ማዘመን ይጠበቅባቸዋል" ብለዋል፡፡
ይህን ለማድረግ ደግሞ መገናኛ ብዙኃኑ ከነባር አሠራራቸው ባሻገር አዲሱ ሚዲያን አቀናጅተው መሄድ እንደሚጠበቅባቸው በመጠቆም።
ዛሬን ጨምሮ ለአራት ቀናት በተዘጋጀው ሥልጠና ላይ ጋዜጠኞች፣ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎችና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ተገኝተዋል፡፡