ቀጥታ፡

ለምስራቅ አፍሪካ አገራት አገልግሎት በመስጠት የውጭ ምንዛሬ ማምጣት የሚያስችል ተቋማዊ አቅም እየተፈጠረ ነው - የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት

አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 18/2015 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት ለምስራቅ አፍሪካ አገራት አገልግሎት በመስጠት የውጭ ምንዛሬ ማምጣት የሚያስችል ተቋማዊ አቅም እየፈጠረ መምጣቱን ገለፀ።

የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት ዓለም አቀፍ እውቅና ያለው የፍተሻ፣ የቁጥጥርና የእውቅና ማረጋገጫ አገልግሎቶች ጂቡቲን ጨምሮ በአዲስ አበባና በክልል በሚገኙ ዘጠኝ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች እየሰጠ ይገኛል።

ድርጅቱ ምርትና አገልግሎቶች ዓለም አቀፋዊ፣ አህጉራዊና አገራዊ እንዲሁም ሌሎች ደረጃዎች ላይ የተቀመጡ የጥራት መስፈርቶች የማረጋገጥ ሥራም ይሰራል።

በመሆኑም በድርጅቱ የፍተሻ፣ የቁጥጥርና የእውቅና ማረጋገጫ አግኝተው የጥራት ደረጃቸውን ጠብቀው ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የኢትዮጵያ ምርቶች በዓለም ገበያ ተቀባይነት እያገኙ መጥተዋል።

የተቋሙን አሁናዊ የሥራ እንቅስቃሴ በተመለከተ ኢዜአ የድርጅቱን የኮርፖሬት ሰርቪስ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ጋሻው ተስፋዬን አነጋግሯል።

ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ በሰጡት አስተያየት፤ የድርጅቱን አቅም ዓለም አቀፍ እውቅና ያለው የፍተሻ፣ የቁጥጥርና የእውቅና ማረጋገጫ አገልግሎቶችን መስጠት የሚችል ተቋም በመፈጠር ማጠናከር ተችሏል ብለዋል።

በዚህም ለምርትና አገልግሎቶች የፍተሻ ላቦራቶሪ እንዲሁም የኢንስፔክሽንና የሰርቲፊኬሽን አገልግሎትን ማዘመን መቻሉን ነው የገለፁት።


 

በመሆኑም ድርጅቱ አሁን ላይ ለምስራቅ አፍሪካ አገራት አገልግሎት በመስጠት የውጭ ምንዛሬ ማምጣት የሚያስችል ተቋማዊ አቅም እየፈጠረ መምጣቱን ነው የተናገሩት።

በዚህም በምስራቅና ደቡብ አፍሪካ አገራት የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) በንግድ ግብዓቶች ላይ የሚኖሩ ክርክሮችን ለመዳኘት መመረጡን ገልፀዋል።

ይህ የተፈጠረውን አቅም በማጠናከር ለአገር የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኝ ተቋም ለመፍጠር በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

ይህን ሥራ ማቀላጠፍ የሚያስችል በዘመናዊ ላቦራቶሪዎች የተደራጀ ግዙፍ የሕንፃ ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸው ግንባታው በሚቀጥለው ዓመት ተጠናቆ አገልግሎት እንደሚጀምር ተናግረዋል።

ምርቶቻቸውንና አገልግሎታቸውን የሚያስፈትሹ ድርጅቶች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን የተናገሩት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ ይህም በተሰራው የግንዛቤ መፍጠር ሥራ ውጤት እየመጣ መሆኑን አመላካች ነው ብለዋል።

ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘውም ድርጅቱ በ2015 በጀት ዓመት 22 ሺህ 334 ለሚሆኑ አገልግሎቶች የጥራት ማረጋገጫ መስጠቱን አስታውቀዋል።

የጥራት ማረጋገጫ የተሰጠው ተቋሙ ዓለም አቀፍ እውቅና ባገኘባቸው 145 የፍተሻ ላቦራቶሪ፣ ኢንስፔክሽንና ሰርተፊኬሽን ወሰኖች የጥራት ማረጋገጫ መሆኑን ገልፀዋል።

የድርጅቱን አቅም በላቦራቶሪ በማጠናከር ጠንካራና ተወዳዳሪ ተቋም በመፍጠር በኢኮኖሚው ጉልህ አስተዋፅዖ እንዲኖረው በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም