ኢትዮጵያና ተርኪዬ በመረጃና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲሁም በአካባቢ ጥበቃ በትብብር ለመስራት ከስምምነት ላይ ደረሱ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያና ተርኪዬ በመረጃና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲሁም በአካባቢ ጥበቃ በትብብር ለመስራት ከስምምነት ላይ ደረሱ
አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 18/2015 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ እና ተርኪዬ በመረጃና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲሁም በአካባቢ ጥበቃ ላይ በትብብር ለመስራት ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።
በጣሊያን ሮም የተባበሩት መንግስታት የዓለም የምግብ ስርዓት ጉባኤ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
ከጉባኤው ጎን ለጎን የኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ጌታሁን ጋረደው(ዶ/ር) ከተርኪዬ የአውሮፓ እና የውጭ ግንኙነት ዋና ዳይሬክተር ፉአት ካሳሚካን አገራቱ በአካባቢ ጥበቃ ያላቸውን ትብብር ማጠናከር በሚችሉባቸው ሁኔታዎች ላይ ተወያይተዋል።
የአካባቢ ጥበቃ፣ የኬሚካል እና አደገኛ ቆሻሻ አያያዝ፣የምግብ ምርት ብክነት ቅነሳ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር እና የሰው ኃይል ልማት ውይይት የተደረገባቸው ጉዳዮች ናቸው።
ዋና ዳይሬክተሩ ኢትዮጵያ በአካባቢ ጥበቃ ዘርፍ እያከናወነች ያለውን ተግባር አስመልክቶ ለዳይሬክተሩ ገለጻ አድርገውላቸዋል።
ኢትዮጵያ በዘርፉ እያከናወነች ያለችውን ስራዎች ተርኪዬን ጨምሮ ሌሎች የልማት አጋሮች እንዲደግፉም ጥሪ አቅርበዋል።
የቱርኪዬ የአውሮፓ እና የውጭ ግንኙት ዋና ዳይሬክተር ፉአት ካሳሚካን በበኩላቸው ሁለቱ አገራት የጋራ ትብብራቸውን ማጠናከር የሚችሉባቸው ሰፊ እድሎች እንዳሉ በማንሳት ግንኙነታቸውን ለማሳደግ መስራት እንደሚገባቸው አመልክተዋል።
በቱርኪዬ ቀዳማዊት እመቤት ኤሚን ኤርዶጋን በሚመራው "የዜሮ ቆሻሻ " ኤኒሼቲቭ አገሪቷ ልምዷን ለማካፈል እንደምትፈልግ ገልጸዋል።
በውይይቱ የመረጃ እና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲሁም የአካባቢ ጥበቃ ላይ በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት የዓለም የምግብ ስርዓት ጉባኤ ነገ ይጠናቀቃል።