የኢዜአ ተቋማዊ ለውጥ ብሔራዊ መግባባት የመፍጠርና የሀገርን ገፅታ በዓለም የማጉላት ተልዕኮውን ለማሳካት አቅም የሚፈጥር ነው -የአዲስ አበባ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ፅሕፈት ቤት ኃላፊ - ኢዜአ አማርኛ
የኢዜአ ተቋማዊ ለውጥ ብሔራዊ መግባባት የመፍጠርና የሀገርን ገፅታ በዓለም የማጉላት ተልዕኮውን ለማሳካት አቅም የሚፈጥር ነው -የአዲስ አበባ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ፅሕፈት ቤት ኃላፊ
አዲስ አበባ ፤ ሀምሌ 18/2015(ኢዜአ)፡- የኢዜአ ተቋማዊ ለውጥ ብሔራዊ መግባባት የመፍጠርና የሀገርን ገፅታ በዓለም የማጉላት ተልዕኮውን ለማሳካት አቅም የሚፈጥር መሆኑን የአዲስ አበባ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ፅሕፈት ቤት ኃላፊ ሞገስ ባልቻ ገለጹ።
የአዲስ አበባ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ፅሕፈት ቤት ኃላፊ ሞገስ ባልቻ እና ሌሎችም አመራሮች የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) አዲሱን የሚዲያ ኮምፕሌከስ ጎብኝተዋል።
ከጉብኝቱ በኋላ ኃላፊው በሰጡት አስተያየትም፤ ኢዜአ አጠቃላይ ተቋማዊ ለውጥ ውስጥ መሆኑንና በተለይም በቴክኖሎጂ የላቀ ደረጃ ላይ መድረሱ እንዳስደነቃቸው ጠቁመዋል።
የ80 ዓመት እድሜ ያለው ኢዜአ በተቋማዊ ለውጡ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች የደረሱበትን የሚዲያ ኮምፕሌክስ ባለቤት መሆኑ ለኢትዮጵያ ገፅታ ትልቅ አስተዋፅኦ ያለውና የሚያኮራ መሆኑን ተናግረዋል።
በሚዲያ ሕንጻና በቴክኖሎጂ የተደረጉ ሥር ነቀል ማሻሻያዎች የተቋሙን ቁመና ወደ ላቀ ደረጃ የሚያደርሱ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ የአገርንና የህዝብን አጀንዳዎች በጥልቀት የሚዳስስ የይዘት ሥራዎች ላይ ማተኮር ይኖርበታል ብለዋል።
ሚዲያ በአገር ግንባታ ሂደት ያልተገቡ ትርክቶችን በመፍጠር አገርን እስከማፍረስ የሚደርስ አሉታዊ ተጽእኖ ንዳለው በተለያዩ አገራት አይተናል ሲሉ ተናግረዋል።
በሌላ በኩል በሚዲያ ደግሞ ጠንካራ አገረ መንግሥት የገነቡና የትርክት የበላይነት የያዙ አገሮች መኖራቸው ልብ ሊባል ይገባል ነው ያሉት።
በኢትዮጵያ አገራዊ ለውጡን ተከትሎ ለሁሉም የምትመችና ብሔራዊ መግባባት የተፈጠረባት ጠንካራ አገርን ለመገንባት እየተሰራ መሆኑን በማንሳት ለዚህ ስኬት የኢዜአ ሚና የላቀ እንደሆነ ጠቁመዋል።
ኢዜአ ያካሄደው ተቋማዊ ለውጥ ብሔራዊ መግባባትን የመፍጠር ተልዕኮውን ለማሳካት አቅም የሚፈጥር መሆኑን በማንሳት፤ ለስኬቱም አዳዲስ አጀንዳዎችን በመቅረፅና የአንድነት ትርክትን በአግባቡ በመቀንበብ ሊሰራ እንደሚገባው አንስተዋል።
የዜና ተቋሙ ቀደም ሲል ያለ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በአገር ግንባታ ሂደት ትልቅ ሚና እንደነበረው አስታውሰው አሁን የደረሰበት ደረጃ ደግሞ የአገር ግንባታንና ብሔራዊ መግባባት ተልዕኮውን በተሻለ መልኩ ለማሳካት የሚያሰችል አቅም ፈጥሮለታል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ትልቅ ታሪክ፣ የተፈጥሮ ኃብትና ብዙ ህዝብ ያላት አገር የመሆኗን ያህል በዓለም አቀፍ መድረኮች ያላት ሥፍራ ከፍ ባለ ደረጃ እንዲቀጥል ኢዜአ ሌላ ድርብ ተልዕኮ እንዳለበትም ጠቅሰዋል።
በሚዲያ ቴክኖሎጂ የደረሰበት አቅም የቀጣናው የሚዲያ ማዕከል መሆን የሚያስችለው ነው ያሉት አቶ ሞገስ በሌሎች አገራት የተያዘውን በሚዲያ የትርክት የበላይነት ለመቀልበስ እንዲሁም የአፍሪካና የሌሎች ወዳጅ አገራት ድምፅ ለመሆን መትጋት አለበት ሲሉ ገልጸዋል።