ኢትዮጵያ ከስዊዘርላንድ ጋር ያላትን የኢኮኖሚ ትብብር ታጠናክራለች-ለሊሴ ነሜ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከስዊዘርላንድ ጋር ያላትን የኢኮኖሚ ትብብር ታጠናክራለች-ለሊሴ ነሜ
አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 18/2015 (ኢዜአ)፡-ኢትዮጵያ ከስዊዘርላንድ ጋር ያላትን የኢኮኖሚ ትብብር ለማጠናከር እንደምትሻ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ኢንጂነር ለሊሴ ነሜ ገለጹ።
ኮሚሽነር ኢንጂነር ለሊሴ ነሜ በስዊዘርላድ አምባሳደር ታማራ ሞና ጋር ተወያይተዋል።
ውይይታቸው በኢትዮጵያ ስላሉ ሳቢ የኢንቨስትመንት እድሎች እና በዘርፉ ያለውን እምቅ አቅም በመጠቀም አገራቱ ያላቸውን ትብብር ማጠናከር በሚችሉባቸው ሁኔታዎች ላይ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል።
ኮሚሽነር ለሊሴ ኢትዮጵያ ከስዊዘርላንድ ጋር በኢኮኖሚው ዘርፍ ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ማጠናከር እንደምትፈልግ እና አገራቱም ትብብራቸውን ለማጎልበት መስራት እንዳለባቸው አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ እና ስዊዘርላንድ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እ.አ.አ 1933 ነው።
በጄኔቫ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ጽህፈት ቤት ኢትዮጵያ ከስዊዘርላንድ ጋር ያላትን የዲፕሎማሲ ግንኙነት ስራዎች የሚሸፍን ሲሆን በአንጻሩ ስዊዘርላንድ እ.አ.አ በ1962 በአዲስ አበባ ኤምባሲዋን ከፍታለች።
ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ የስዊዘርላንድ ከዋንኛ የንግድ አጋሮች ውስጥ በቀዳሚነት ትጠቀሳለች።
ስዊዘርላንድ ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገራት ስትራቴጂ ላይ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የኢኮኖሚ አቅም ያላት በማደግ ላይ የምትገኝ አፍሪካዊት አገር እንደሆነች ይገለጻል።
ሁለቱ አገራት ከኢኮኖሚው በተጨማሪ በልማት፣ በኢኖቬሽን፣ በምርምር፣ በትምህርት እና በሰብአዊ ጉዳዮች መልካም የሚባል ትብብር አላቸው።