ቀጥታ፡

የዓለም የምግብ ስርዓት ማሻሻያ ያስፈልገዋል - አንቶኒዮ ጉቴሬዝ 

አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 18/2015 (ኢዜአ)፡- “ስብራት” የገጠመው የዓለም የምግብ ስርዓት ማሻሻያ እንደሚያስፈልገው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ገለጹ።

“በዓለም አቀፍ ደረጃ ፍትሐዊና ዘላቂ የምግብ ስርዓት ለመፍጠር አዲስና ጠንካራ የግብርና ፋይናንስ ሞዴል ያስፈልጋል” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መግለጻቸው ይታወሳል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የምግብ ስርዓት ጉባኤ በጣልያን ሮም እየተካሄደ ይገኛል።

የተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በጉባኤው መክፈቻ ላይ ያደረጉት ንግግር በዓለም ስላለው የምግብ እህል አቅርቦት ችግር ምላሽ የመስጠት አስፈላጊነት፣ በመንግስታት እና በንግዱ ማህበረሰብ መካከል ያለውን ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ እና የአየር ንብረት ለውጥ በምግብ ምርታማነት ላይ እያሳደረ ያለውን ተጽእኖ መከላከል ላይ ትኩረቱን አድርጓል።

“ሰዎች በረሃብ ሲሰቃዩ እና ሲሞቱ ማየት በጣም አሰቃቂ እና አሳዛኝ ነው፤ የዓለም የምግብ ስርዓት ተሰብሯል በዚህም ምክንያት በቢሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ከፍተኛ ዋጋ እየከፈሉ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።

እንደ ተመድ ትንበያ በዓለም ላይ ከ780 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ረሃብ እንደሚያስተናግድ እና ይህም በዓለም ከ10 ሰው 1 ሰው በረሃብ ተጽእኖ ውስጥ ነው።

በማደግ ላይ የሚገኙ አገራት ባላቸው ውስን ሀብቶች እና የእዳ ጫና ምክንያት በምግብ ስርዓታቸው ላይ በሚፈለገው ደረጃ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዳያፈሱ እጅ አጥሯቸዋል ብለዋል።

ይህም አገራት በተለይ ለዜጎች የተመጣጠነ ምግብ ለማቅረብ እጅጉን ፈታኝ አድርጎባቸዋል ሲሉም ጠቅሰዋል።
ስለሆነም ይላሉ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የተሰበረውን የምግብ ስርዓት በማሻሻል የምግብ አመራረት እና አጠቃቀምን ፍትሐዊ እና ሚዛናዊ ማድረግ ይገባል።

ዋና ፀሐፊው ከዚህ አኳያ ሶስት ቁልፍ ያላቸውን እርምጃዎች አንስተዋል።

ከፍተኛ ገንዘብ በዘላቂ የምግብ ስርዓቶች ላይ ፈሰስ ማድረግ የመጀመሪያው መፍትሔ እንደሆነ ገልጸዋል።
“የምግብ ስርዓት ኢንቨስትመንትን ማስራብ ዜጎችን እንደ ማስራብ ይቆጠራል” ያሉት ዋና ፀሐፊው መንግስታት በዘላቂ ልማት ግቦች የተቀመጠውን የገንዘብ ድጋፍ ማዕቀፍ ተግባራዊ በማድረግ በየዓመቱ አገራት የሚያስፈልጋቸውን 500 ቢሊዮን ዶላር እንዲሰጡ ጠይቀዋል።

እንደ ሁለተኛ መፍትሔ ያስቀመጡት ሀሳብ መንግስታት እና የንግድ ተቋማት “ከትርፍ ይልቅ ሰውን ያስቀደመ” የምግብ ስርዓት መገንባት አለባቸው የሚል ነው።

ሁሉም ዜጎች ጤናማ ምግብ የሚያገኙበትን አዳዲስ መንገዶች መፍጠር በሶስተኛ ደረጃ በጉተሬዝ የተቀመጠው የመፍትሔ አማራጭ  ሲሆን አገራት የምግብ ገበያቸውን ክፍት እንዲያደርጉ እንዲሁም የንግድ እና የኤክስፖርት ገደቦች እንዲያነሱ ጠይቀዋል።

የዓለም አገራት ፍትሐዊ የምግብ ስርዓት ለመገንባት በቁርጠኝነት መስራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

የተባበሩት መንግስታት የምግብ እና እርሻ ድርጅት(ፋኦ) ዋና ዳይሬክተር ኩ ዶንግዩ በበኩላቸው የዓለም የምግብ ስርዓትን ዘላቂ፣ ሁሉን አካታች፣ የማይበገር እና ተወዳዳሪ በሆነ መልኩ መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል።

በዘላቂ ልማት ግቦች ግብ 17 ላይ የተቀመጠውን የምግብ ዋስትና የማረጋገጥ ጉዳይ የሚሳካው በዓለም የምግብ ስርዓት ላይ ለውጥ ማምጣት ሲቻል መሆኑ በመግለጽ።

የስርዓቱ አካታችነት የተሻለ ምርታማነት፣ የተሻለ የተመጣጠን ምግብ አቅርቦት፣ የተሻለ ከባቢ አየር ለመፍጠር እና ዘላቂ የሆነ የግብርና ስርዓት ለመገንባት እንደሚያስችል ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር በዓለም አቀፍ ደረጃ ፍትሃዊና ዘላቂ የምግብ ሥርዓት ለመፍጠር አዲስና ጠንካራ የግብርና ፋይናንስ ሞዴል እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል። 

ከዚህ ጎን ለጎንም የግብርና ምርቶች የገበያ እድል እንዲያገኙና የዘርፉ እሴት ሰንሰለት እንዲጠናከርም መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

በተለይ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የሚከሰተውን ዓለም አቀፍ የምግብ እጥረት ቀውስ ለመከላከል አገራት በጋራ መስራት አለባቸው ብለዋል።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም