ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ያዘጋጀችውን የሥርዓተ- ምግብ ሽግግር ፍኖተ-ካርታ ሙሉ በሙሉ ገቢራዊ በማድረግ ምሳሌ ለመሆን እየሰራች ነው - ዶክተር ግርማ አመንቴ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 17/2015 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ያዘጋጀችውን የሥርዓተ- ምግብ ሽግግር ፍኖተ-ካርታ ሙሉ በሙሉ ገቢራዊ በማድረግ ምሳሌ ለመሆን እየሰራች መሆኑን የግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ ገለጹ። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በጣሊያን ርዕሰ መዲና ሮም ከተማ በተካሄደው የተባበሩት መንግሥታት የምግብ ሥርዓት ጉባኤ ላይ ተሳትፈዋል። 

ከዚህ ጎን ለጎን የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ግርማ አመንቴ እንደተናገሩት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሥርዓተ-ምግብ ሽግግር ከሁለት ዓመታት በፊት በአሜሪካ ኒውዮርክ የተጀመረ ነው።

በኒው ዮርኩ ስብሰባ ኢትዮጵያ የሥርዓተ-ምግብ ሽግግር ፍኖተ-ካርታ ማቅረቧን አስታውሰዋል።  

ኢትዮጵያ አዘጋጅታ ያቀረበችው የሥርዓተ-ምግብ ሽግግር ፍኖተ-ካርታ የተዋጣለት የሚባል መሆኑን በመድረኩ መነሳቱን ጠቅሰዋል።  

የዛሬው ጉባኤም ከሁለት ዓመት በኋላ ምን ተሰራ የሚለው የሚታይበት መሆኑን ነው ያነሱት።

ፍኖተ ካርታውን ለመተግበር አስፈላጊው ዝግጅት ሲካሄድ መቆየቱን ጠቁመው ከዝግጅቶቹ መካከል አደረጃጀቶችን የመፍጠር ሥራ የሚጠቀስ ነው ብለዋል። 

በዚህም አስራ አምስት ሚኒስትሮች ያካተተ ኮሚቴ መዋቀሩን ገልጸው፤ ኮሚቴውን የግብርና ሚኒስቴርና የጤና ሚኒስቴር በጋራ እንደሚመሩት አስረድተዋል። 

በክልል ደረጃና በዘርፉ በጋራ የሚሰሩ አጋር አካላትም ተመሳሳይ አደረጃጀት እንደሚኖር ጠቁመዋል። 

በዘንድሮው የተባበሩት መንግስታት የምግብ ሥርዓት ጉባኤ ላይም የኢትዮጵያ ሪፖርት የተሻለ ተብሎ የቀረበ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከፍኖተ-ካርታው ጋር አገራዊ ኢኒሼቲቮች እንዴት ይጣጣማሉ የሚለውን ለማወቅ ጥናት ተደርጎ ጥናቱ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን አንስተዋል። 

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ፍኖተ-ካርታውን ወደ ትግበራ የሚያስገባ ዝርዝር የድርጊት መርሃ ግብር በመቅረጽ ላይ እንደምትገኝ ነው የገለጹት።  

የሥርዓተ-ምግብ ሽግግር ከምርት እስከ ማዕድ ያለውን አጠቃላይ ሂደት በተለይም ምግብ ተመርቶ ሳይባክንና ደኅነነቱ እንደተጠበቀ ተጠቃሚ ጋር የማድረስ ጉዳይ በመሆኑ ትኩረት እንደሚሻ በጉባኤው ተነስቷል ብለዋል።  

የምግብ ጉዳይ ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው በመሆኑ ኢትዮጵያም የስርዓተ ምግብ ሽግግር ላይ በትኩረት እንደምትሰራ ጠቁመዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም