ቀጥታ፡

የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ እና የሪፐብሊካን ጥበቃ ኃይል የሰራዊት አባላት ተደማሪ ደማቅ ታሪክ ለመጻፍ ሁሌም ዝግጁ መሆን አለባቸው - ጄነራል አበባው ታደሰ

አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 17/2015 (ኢዜአ):- “የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ እና የሪፐብሊካን ጥበቃ ኃይል የሰራዊት አባላት ለኢትዮጵያ በከፈሉት ዋጋ ተጽፎ የማያልቅ ታሪካቸው ላይ ተደማሪ ታሪክ ለመጻፍ ሁሌም መዘጋጀት ይገባቸዋል” ሲሉ የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰ ገለጹ፡፡

የሁለቱ ክፍል አመራሮች በጋራ ዓመታዊ የስራ አፈጻጸም ማጠቃለያ ውይይት አድርገዋል።


 

የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰ “በውጊያ የበላይነት ለመያዝ ሁሌም የማያቋርጥ የኃይል ዝግጅት ማድረግና የሞራልና የሐሳብ የበላይነት በመያዝ በጠንካራ ወታደራዊ ሳይንስ ሁሉንም አደረጃጀቶች አቀናጅቶ መምራት ለድል አስፈላጊና ወሳኝ ነው” ብለዋል።

የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ እና የሪፐብሊካን ጥበቃ ኃይል ውጊያዎችን በማረም፣ በማስተካከል እና አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በመቀየር “ወደር የሌለው” ውጤት ማስመዝገባቸውን ገልጸዋል።

ወታደር ካለፈ ታሪክ ይማራል እንጂ ባለፈ ታሪክ አይኖርም፤ ስለዚህ ካለፈው ታሪካቸው በመማር ሁለቱም ክፍሎች ለላቀ ድል መዘጋጀት አለባቸው ብለዋል።

ሁለቱም ክፍሎች ያስመዘገቡት ውጤት ከላይ እስከ ታች ባለው የአመራሩ እና የአባላቱ ጠንካራ ቅንጅት የተገኘ ድል መሆኑን አመልክተዋል።

ስለሆነም ይህንን ጥንካሬ እና የተናበበ ቅንጅት በመጠበቅ ተጽፎ በማያልቀው ታሪካቸው ላይ ተደማሪ ታሪክ ለመጻፍ ሁሌም ዝግጁ መሆን ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ፡፡

ኢትዮጵያ እና ሕዝቦቿ እንዲሁም መንግስት ለአገር መከላከያ ሰራዊት የላቀ ክብር እንዳላቸው ገልጸው ሰራዊቱም የተጣለበትን አገራዊ ተልዕኮ በፅናት እየተወጣ እንደመጣው ሁሉ አሁን ላይም የሚሰጠውን አገራዊ ግዳጅ በውጤት መፈጸም እንደሚገባው አስገንዝበዋል።


 

የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ሹማ አብደታ በበኩላቸው ዕዙ በየደረሱበት ሁሉ ሁኔታዎችን በፍጥነት በመቀየር አገርና ሕዝብን ያኮራ ታሪክ መፈጸሙን መግለጻቸውን ከኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም