ቀጥታ፡

በሀዋሳ ከተማ ዓመታዊው የቅዱስ ገብርኤል ንግሥ በዓል በሰላም እንዲከበር  ዝግጅት  ተደርጓል -ፖሊስ

ሀዋሳ ፤  ሐምሌ 17 /2015 (ኢዜአ) ፡- በሀዋሳ ከተማ ዓመታዊው የቅዱስ ገብርኤል ንግሥ በዓል በሰላም እንዲከበር ከፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ሰላምና ደህንነትን  ለማስከበር ዝግጅት  መደረጉን ፖሊስ አሰታወቀ ። 

የበዓሉን ሰላምና ደህንነት ማስከበር በሚቻልበት ዙሪያ  የጸጥታ አካላት ዛሬ በሀዋሳ ከተማ ተወያይተዋል።

በዚህ ወቅት የሲዳማ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሽመልስ ቶማስ፤ ሐምሌ 19 ቀን 2015 የሚከበረው ዓመታዊው የቅዱስ ገብርኤል ንግስ  በዓሉን በማስመልከት ከእምነቱ ተከታዮችና ሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት ለመስራት ዝግጅቱን አጠናቀናል ብለዋል። 

በተለይ ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከደቡብ ሬጅመንት፣ ከመከላከያ ሠራዊት፣ ከደቡብ ዕዝ መምሪያ፣ ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት እንዲሁም  ከክልሉ  ፖሊስ ኮሚሽን የተውጣጣ ግብረ ኃይል በጋራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በፖሊስ ሊደረጉ የሚገቡ የቁጥጥር፣የፍተሻና ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲኖር ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር በቅንጅት ለመስራት በቂ ዝግጅት መደረጉን ኮሚሽነር ሽመልስ ተናግረዋል።

በከተማዋ በተለያዩ አካባቢዎች የፖሊስ ማዕከላትን በማቋቋም ከህብረተሰቡ ጋር በቅርበት ለመስራት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ጠቁመዋል።

በዓሉን ለማክበር ወደ ሀዋሳ የሚገቡ እንግዶችና ጎብኚዎች ቁጥር ከወትሮው በተለየ መልኩ ሊጨምር ስለሚችል ወደ ከተማዋ መግቢያና መውጫ በሮች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እንደሚደረግም ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል።

በተለይ ከነገ ከሰዓት በኋላ ጀምሮ እስከ በዓሉ ፍጻሜ ድረስ በከተማዋ ወደ ቅዱስ  ገብርዔል ቤተክርስቲያን የሚወስዱ ዋና ዋና መንገዶች የትራፊክ እንቅስቃሴ ገደብ ስለሚጣል አሽከርካሪዎች  አማራጭ መንገዶችን እንዲጠቀሙ አሳስበዋል።

በፌዴራል ፖሊስ የደቡብ ሪጅን ደቡብ መምሪያ ሬጅመንት ሶስት አዛዥ ኮማንደር አድና ናስር በበኩላቸው፤ ሠራዊቱ የበዓሉን ሰላማዊነት ለማረጋገጥ  ከክልሉና ከከተማዋ አስተዳደር የጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንና በተለይ በዓሉን ለመታደም የሚመጡ እንግዶችንና የንግስ ቦታዎችን ደህንነት ለመጠበቅ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።

በሀገር መከላከያ ሠራዊት የደቡብ ዕዝ ጠቅላይ መምሪያ ተወካይ ሌተና ኮሎኔል ደረጀ በዴቻ ፤ በከተማዋ የሚከበረው የቅዱስ ገብርዔል ንግስ በዓልን ደህንነት ለማረጋገጥ  ሠራዊቱ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል  ብለዋል።

በዓሉ ተከብሮ ምዕመናን ወደ መጡበት እስኪመለስ ድረስ ከክልሉና ከፌዴራል የጸጥታ አካላት ጋር በጋራ እንደሚሰሩም ገልጸዋል።

 የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ሃላፊ ኢንስፔክተር መልካሙ አየለ ፤ በዓሉ ካለምንም የፀጥታ ችግር በሰላም እንዲከበር  ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን አመልክተዋል። 

በከተማዋ ሁሉም ክፍለ ከተሞች 24 የፖሊስ መቆጣጠሪያ ጣቢያዎች እንደተገነቡና በነዚህ ስፍራዎች የጥቆማ ማዕከላትም መቋቋማቸውን አስታውቀዋል።

በተለይ በከተማዋ ዋና ዋና መንገዶች ዘመናዊ ካሜራዎች መተከላቸውንና ማንኛውንም እንቅስቃሴ በካሜራ በመታገዝ ቁጥጥርና ክትትል እንደሚደረግ ነው ሃላፊው የገለጹት።

 ህብረተሰቡ በበዓሉ ላይ የተለየ ነገር በሚያጋጥመው ወቅት በአቅራቢያው በሚገኝ የፖሊስ መቆጣጠሪያ ጣቢያ በማሳወቅ አልያም በስልክ ቁጥር 0462209164 በመደወል መረጃ በመስጠት እንዲተባበር ጠይቀዋል።

 

 

 

 

 

   

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም