ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ እና ፓኪስታን የንግድና ኢኮኖሚ ግንኙነት ይበልጥ መጠናከር ይኖርበታል- ፕሬዝዳንት አሪፍ አልቪ

አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 17/2015 (ኢዜአ):- የኢትዮጵያ እና ፓኪስታን የንግድና ኢኮኖሚ ግንኙነት ይበልጥ መጠናከር እንደሚገባው የአገሪቷ ፕሬዝዳንት ዶክተር አሪፍ አልቪ ገለጹ።

ፕሬዝዳንት አሪፍ በኢትዮጵያ የፓኪስታን አምባሳደር ሆነው ከተሾሙት ሚያን አቲፍ ሸሪፍ ጋር ተወያይተዋል።

በውይይቱ ፕሬዝዳንቱ ሁለቱ አገራት ያላቸው ግንኙነት በጋራ ታሪክ እና ፍላጎቶች ላይ የተመሰረተ መሆኑንና በዓለም አቀፍ መድረክ በትብብር እየሰሩ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ይህ የአገራቱ ግንኙነት በኢኮኖሚ እና ንግድ መስኮች ይበልጥ መጎልበት እንደሚገባውም አመልክተዋል።

የአገራቱን የንግድ ልውውጥ መጠን ለማሳደግ ከኢትዮጵያ የንግድ ማህበረሰብ ጋር በትብብር መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው በዘርፉ ያለውን አቅም አሟጦ መጠቀም እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

በተጨማሪም የሁለቱን አገራት ትብብር በትምህርት እና በሕዝብ ለሕዝብ ትስስር ይበልጥ ማሳደግ እንደሚቻል ነው ፕሬዝዳንቱ ያነሱት።

የፓኪስታን የውጭ አገልግሎት አካዳሚ የኢትዮጵያ ወጣት ዲፕሎማቶችን የማሰልጠንና በባንክ ዘርፍ ላሉ ትምህርቶች ለመስጠት ያሳየችው ፍላጎት ነጻ የትምህርት እድል የሁለቱን አገራት ትብብር ይበልጥ እንደሚያሳድጉት ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ እና ፓኪስታን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እ.አ.አ በ1958 ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም