እስራኤል በጤናው ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር እየሰራች ያለውን ሥራ አጠናክራ ትቀጥላለች- በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር - ኢዜአ አማርኛ
እስራኤል በጤናው ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር እየሰራች ያለውን ሥራ አጠናክራ ትቀጥላለች- በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 17/2015(ኢዜአ)፦ እስራኤል በጤናው ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር እየሰራች ያለውን ሥራ አጠናክራ እንደምትቀጥል በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አለልኝ አድማሱ ተናገሩ።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ እስራኤል ከሚገኘው "ሴቭ ቻይልድስ ኸርት" ከሚባል ግብረ- ሰናይ ድርጅት ጋር ያለውን ትብብር ለማጠናከር የሚያስችለውን ስምምነት አድርጓል።
ስምምነቱ የልብ ሕሙማን ህፃናት በእስራኤል አገር ሕክምና እንዲያገኙ የሚደረገውን ሥራ የሚያጠናክር መሆኑ ተገልጿል።
በዚሁ ወቅት በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አለልኝ አድማሱ፤ አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ረዥም ዓመት ያስቆጠረ ግንኙነት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ዘርፈ-ብዙ ግንኙነት በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ መስክ ላይ ያተኮረ መሆኑን አምባሳደሩ ተናግረዋል።
በተለይ በጤናው ዘርፍ የኢትዮጵያ ባለሙያዎችን የማሰልጠንና የሰው ኃይሉን የማብቃት ሥራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን ጠቁመዋል፡፡
በተለይ ህፃናት በልብ ሕመም ለሞት እንዳይዳረጉ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን በማንሳት፤ ለአብነትም ታካሚዎች ወደ እስራኤል ሄደው እንዲታከሙ መደረጉን ጠቁመዋል።
በልብ ሕመም የሚሰቃዩ ህፃናትን ህይወት ለመታደግና ወደ መልካም ጤንነት እንዲመለሱ ለማድረግ እንሰራለን ብለዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር አንዱአለም ደነቀ በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው በልብ ቀዶ ሕክምና ዙሪያ ከእስራኤል ሐኪሞች ጋር ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰዋል።
የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ባለሙያዎች በልብ ሕክምና እንዲሁም በልብ ቀዶ ሕክምና ዙሪያ አቅማቸውን የሚያሳድግ ሥልጠና ያገኛሉ ብለዋል።
የሴቭ ቻይልድስ ኸርት ዋና ዳይሬክተር ሳይመን ፊሸር በበኩላቸው፤ በስምምነቱ በመታገዝ በዓመት 20 የልብ ሕሙማን ህፃናት በእስራኤል አገር ሕክምና እንዲያገኙ ይደረጋል ብለዋል።
ለህፃናቱ ከሚደረገው ሕክምና በተጨማሪ በዘርፉ ለሚሰሩ ባለሙያዎች ሥልጠና እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
የጤና ሳይንስ ኮሌጁ ከድርጅቱ ጋር የነበረው ስምምነት በኮቪድ-19 ምክንያት ተቋርጦ መቆየቱን አስታውሰው፤ የተደረገው ስምምነት የቀደሞውን ትብብር የሚያድስ ነው ብለዋል።