አሰልጣኝ ውበቱ አባተ የፋሲል ከነማ አሰልጣኝ ሆኖ ተሾመ - ኢዜአ አማርኛ
አሰልጣኝ ውበቱ አባተ የፋሲል ከነማ አሰልጣኝ ሆኖ ተሾመ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 17/2015(ኢዜአ)፦የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በይፋ የፋሲል ከነማ አሰልጣኝ በመሆን ተሹሟል።
የፋሲል ከነማ ክለብ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ለሦስት ዓመት ኮንትራት ክለቡን ለማሰልጠን ነው ውል የተዋዋለው።
የጎንደር ከተማ ከንቲባና የክለቡ ፕሬዝዳንት ባዩህ አቡሃይ በዚህ ወቅት፤ ፋሲል ከነማ ለቀጣዩ አምስት ዓመት በሀገር ውስጥና በምስራቅ አፍሪካ ተወዳዳሪ ክለብ እንዲሆን የሚያስችል ዕቅድ ወጥቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ክለቡ በ2015 ዓ.ም የቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊግ የውድድር ዘመን መጠነኛ የውጤት መቀዛቀዝ ታይቶበት እንደነበር ገልጸው፤ ይህንንም በመገምገም የተሻለ ቡድን ለመገንባት ልምድ ያላቸው አሰልጣኝ መቅጠራቸውን ነው የገለጹት።
አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ቡድኑን በ2016 ዓ.ም ጠንካራ ተወዳዳሪ እንዲሆንና በ2017 ዓ.ም ደግሞ ለሻምፒዮንነት እንዲያበቃው ነው የምንጠብቀው ብለዋል።
አሰልጣኙ ከዋናው ቡድን በተጨማሪ ታዳጊዎችን ማብቃት ላይ እንዲያሰለጥን ጭምር ስምምነቱ ያካተተ መሆኑ ተገልጿል።
የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በበኩሉ፤ ከብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝነት ሥራውን ከለቀቀ በኋላ ከሌሎች ክለቦች ጋር በኮንትራት ውል ቀርቦለት እንደነበርና እንዳልተቀበለው ገልጿል።
ከሌሎች ክለቦች የተሻለ አብሮ ሊያሰራ የሚችሉ ጉዳዮች በመኖራቸው ከፋሲል ከነማ ጋር ውል እንዲያስሩ እንዳደረጋቸው ነው የገለጸው።
ከክለቡ ጋር ባለው የውል ዘመን የተቀመጡ ዕቅዶችን ለማሳካት እንደሚሰራም ነው የተናገረው።