ቀጥታ፡

ዳያስፖራው በሀገር ቤት በኢንቨስትመንትና ቢዝነስ ላይ ተሳትፎውን እንዲያሳድግ ጥሪ ቀረበ

 

አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 17/2015 (ኢዜአ) :- ዳያስፖራው በሀገር ቤት በኢንቨስትመንትና ቢዝነስ ላይ ተሳትፎውን እንዲያሳድግ በደቡብ አፍሪካ የኢፌዴሪ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሙክታር ከድር(ዶ/ር) ጥሪ አቀረቡ።

ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት የተውጣጣ ልዑክ በደቡበ አፍሪካ የሚገኙ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የልማት ተቋማት የሥራ እንቅስቃሴ ላይ የመስክ ምልከታ አካሂዷል፡፡

በወቅቱም በሃውቴንግ ፕሮቪንስ ዌስትራንድ-ራንድፎንቴይን በሚገኝ የዳያስፖራ የቢዝነስ ማዕከል የሥራ እንቅስቃሴን ልዑኩ ተዘዋውሮ ተመልክቷል፡፡


 

ማዕከሉ በከፍተኛ ካፒታል የሸቀጣ ሸቀጥ ማከፋፈያ ቢዝነስ ዘርፍ ለኢትዮጵያውያንና ደቡብ አፍሪካውያን የሥራ ዕድል የፈጠረ መሆኑን ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

ልዑኩ ተቋሙ እያከናወነ ያለው ተግባር የሀገርንና የዜጎችን መልካም ገጽታ ከፍ ያደረገና በተምሳሌትነት የሚወሰድ መሆኑም ተገልጿል፡፡


 

በወቅቱም አምባሳደሩ ባስተላለፉት መልዕክት በሀገር ውስጥ መንግስት ለዳያስፖራው ያመቻቻቸውን የኢንቨስትመንትና የቢዝነስ አማራጮችን በመጠቀም ወደ ስራ የገቡ ዳያስፖራዎችን አመስግነዋል፡፡

የዳያስፖራ አባላትና ተቋማት በሀገር ቤት ያላቸውን የኢንቨስትመንት ተሳትፎ እንዲያሳድጉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም