ቀጥታ፡

አረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ሥነ-ምህዳርን በመጠበቅ ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ ነው - የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን 

አዲስ አበባ ፤ ሀምሌ 17/2015(ኢዜአ)፡- አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የደን ሽፋንና የከርሰ ምድር ውሃ ክምችትን በመጨመር እንዲሁም ብዝሃ ሕይወትን በመጠበቅ ተጨባጭ ለውጥ እያስገኘ መሆኑን የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ገለጸ።  

የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታሁን ጋረደው ለኢዜአ እንደተናገሩት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በደን ኃብት ላይ ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ ነው።

የዓለም ዋና ዋና ችግሮች ለሆኑት የአየር በክለት፣ የብዝሃ ህይወት መመናመንና የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖ ምላሽ ለመስጠት የአረንጓዴ አሻራ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህንንም ተከትሎ በመጀመሪያው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 25 ቢሊየን ችግኝ መተከሉን ጠቁመው ይህም ለአገሪቱ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳለው ነው ያነሱት።

የተተከለው ችግኝ ካለው ከፍተኛ ቁጥር አንጻር የደን ሽፋንን በማሳደግ፣ የከርሰ ምድር ውሃ ክምችትን በመጨመርና ብዝሃ ሕይወትን በመጠበቅ ፋይዳቸው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

መርሃ ግብሩ የደን ሽፋን እንዲጨምር ከማድረግ ባለፈ ለምግብነት የሚውሉ ችግኞችን የሚያካትት በመሆኑ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታውም ከፍተኛ መሆኑን ነው ያስረዱት።  

በመርሃ ግብሩ  አዳዲስ ችግኞች እንዲተከሉ ከማድረግ ውጪ በሚሰራው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ የደን አካባቢን ከሰውና ከእንሰሳ ንክኪ መጠበቅ መቻሉን ጠቁመዋል። 

ያም ብቻ ሳይሆን በየአካባቢው ነባር ደኖች እንዲያገግሙ ማድረግ መቻሉንም ገልጸዋል። 

ባሳለፈነው ሰኔ ወር/2015 ዓ.ም የተጀመረው ሁለተኛው ምዕራፍ አረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ለቀጣዮቹ አራት ዓመታት የሚቀጥል ሲሆን በዚህም 25 ቢሊየን ችግኝ ለመትከል መታቀዱ ይፋ ተደርጓል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም