ቀጥታ፡

ተሰርቀው የተከማቹ የመሰረተ ልማት ገመዶች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 17/2015(ኢዜአ) :- ተሰርቀው የተከማቹ በርካታ የመሰረተ ልማት ገመዶች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ።

በቁጥጥር ስር የዋሉት ገመዶች ከተለያዩ ቦታዎች ተሰርቀው በአንድ ግለሰብ አማካኝነት ተሸሽገው የተቀመጡ እና የተለያዩ ተቋማት ለመሰረተ ልማት ዝርጋታ የሚጠቀሙባቸው እንደሆኑም ነው ፖሊስ የገለጸው፡፡

በልደታ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የባልቻ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ በአጠራጣሪ ሁኔታዎች መነሻነት በክፍለ ከተማው ወረዳ 10 ላቦራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ጥናት እና ክትትል ሲያደርግ መቆየቱም ተገልጿል፡፡

በእዚህም በሰዋራ ስፍራ በሚገኝ ጠባብ ክፍል ውስጥ በህግ አግባብ ባከናወነው ብርበራ ለመሰረተ ልማት ዝርጋታ የሚውሉ በርካታ ገመዶች ተይዘዋል ነው ያለው ፖሊስ፡፡


 

ከተያዙት ገመዶች መካከል የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮ ቴሌኮም እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ተቋማት የሚገለገሉባቸው ንብረቶች ይገኙበታልም ብሏል፡፡

ገመዶቹን በመሸሸግ ወንጀል የተጠረጠረ አንድ ግለሰብ በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተደረገበት መሆኑንም ፖሊስ ጨምሮ አስታውቋል፡፡

በመሰረተ ልማቶች ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ተጎጂ የሚያደርጉት ብዙሃኑን ህዝብ በመሆኑና በውጪ ምንዛሬ የሚገቡ ከመሆናቸው አንፃር እንደ ሀገር ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ የሚያስከትሉ በመሆኑ ህብረተሰቡ የተሰረቁ የመሰረተ ልማት ዕቃዎችን ባለመግዛትም ሆነ በሚፈፀሙ ወንጀሎች ዙሪያ የሚኖረውን መረጃ ለፖሊስ በመስጠት የድርሻውን እንዲወጣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠይቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም