የሩሲያ-አፍሪካ ጉባኤ በዚህ ሳምንት በቅዱስ ፒተርስበርግ ከተማ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
የሩሲያ-አፍሪካ ጉባኤ በዚህ ሳምንት በቅዱስ ፒተርስበርግ ከተማ ይካሄዳል
አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 17/2015(ኢዜአ) :- ሁለተኛው የሩሲያ-አፍሪካ ጉባኤ እና የሩሲያ-አፍሪካ የኢኮኖሚና ሰብአዊ ፎረም ሐምሌ 20 እና 21/2015 በቅዱስ ፒተርስበርግ ከተማ ይካሄዳል።
ጉባኤው “ለሰላም፣ ደህንነት እና ልማት” በሚል መሪ ሀሳብ የሚከናወን ሲሆን ሩሲያ እና አፍሪካ ያላቸውን “ሁሉን አቀፍ እና ሚዛናዊነት” ላይ የተመሰረተ የሁለትዮሽ ትብብር ማጠናከር አላማ ማድረጉ ተገልጿል።
በሩሲያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ቻም ኡጋላ ኡሪያት ሩሲያ ለአፍሪካ በዓለም አቀፍ መድረክ እያደረገች ያለው ድጋፍ መቀጠሉንና ጉባኤው ከአፍሪካ ጋር በመከባበር ላይ የተመሰረተ ትብብር ለመፍጠር ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው ብለዋል።
ጉባኤው አፍሪካ እና ሩሲያ በኢኮኖሚው ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ይበልጥ የሚያጠናክር መሆኑን ገልጸዋል።
ጉባኤው ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ሁኔታ በፍጥነት እየተቀየረበት ያለበት ወሳኝ ወቅት ላይ እንደሚካሄድ የገለጹት አምባሳደሩ የዓለም አገራት እጣ ፋንታ በራሳቸው እጅ ላይ ነው ብለዋል።
የመጀመሪያው የሩሲያ-አፍሪካ የኢኮኖሚ እና የሰብአዊ ጉዳዮች ፎረም እ.አ.አ በ2019 በሶቺ ከተማ መካሄዱ የሚታወስ ነው።