ቀጥታ፡

የአሳይታ-አፋምቦ-ጅቡቲ ድንበር መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት አፈጻጸም 86 በመቶ ደርሷል-የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር

አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 17/2015(ኢዜአ) :- በፌዴራል መንግስት በተመደበ ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ ውጪ እየተገነባ ያለው የአሳይታ-አፋምቦ-ጅቡቲ ድንበር መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት አፈጻጸም 86 በመቶ መድረሱን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አስታወቀ።

ይህ የመንገድ ፕሮጀክት ወደ ጅቡቲ ለመሄድ አገልግሎት በመስጠት ላይ ከሚገኘው የጋላፊ መስመር በተጨማሪ እንደ አማራጭ ሆኖ የሚያገለግል መሆኑም ከአስተዳደሩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የፕሮጀክቱ ግንባታ 86 በመቶ መጠናቀቁንና ቀሪ ስራዎችን በቅርቡ ለማጠናቀቅ እየተሰራ እንደሚገኝም አስተዳደሩ አመልክቷል።

መንገዱ 50 ኪሎ ሜትር ርዝመት እንዳለውና ከኢትዮጵያ መንግስት በተመደበ ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተጠቁሟል።

መንገዱ በዋናነት ኢትዮጵያን በአሳይታ በኩል ከጅቡቲ ጋር በቅርበት እንደሚያስተሳስር እና አሳይታ ዞንን ከአፋምቦ ወረዳ ብሎም በርካታ ወረዳዎችን እርስ በእርስ በማገናኘት የሕዝብ ለሕዝብ ትስስሩን ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚያግዝም ተገልጿል።

መንገዱ የሚሰራበት አካባቢ የአዋሽ ወንዝ ተፋሰስ የሚገኝበት መስመር እንደ ጥጥ፣ ቴምር፣ ሰሊጥ፣ ቲማቲም፣ ሽንኩርት፣ ብርቱካን እና በርካታ ፍራፍሬዎች የሚመረቱበት በመሆኑ ምርቶች በቀላሉ ወደ ማዕከላዊ ገበያ ብሎም ወደ ጀቡቲ ለማድረስ እንደሚያግዝ ተመላክቷል።

በአካባቢው ከዚህ ቀደም ደረጃውን የጠበቀ የመንገድ መሰረተ ልማት ያልነበረ በመሆኑ ሕብረተሰቡ ቀልጣፋ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዳያገኝ ችግር ፈጥሮ እንደነበር ነው የተጠቆመው።

በመሆኑም ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ከዚህ ቀደም ይስተዋል የነበረውን ችግር በመቅረፍ ቀልጣፋ የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት ያስችላል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም