ቀጥታ፡

መንግስት ጀግናው አትሌት አበበ ቢቂላ በሮም ከተማ መታሰቢያ እንዲኖረው በማድረግ ረገድ ውጤታማ የዲፕሎማሲ ስራ አከናውኗል-ዶክተር ለገሰ ቱሉ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 16/2015(ኢዜአ)፦መንግስት ጀግናው አትሌት አበበ ቢቂላ በሮም ከተማ መታሰቢያ እንዲኖረው በማድረግ ረገድ ውጤታማ የዲፕሎማሲ ስራ ማከናወኑን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ ገለጹ።

መታሰቢያው የአትሌቱ ታሪክ ተጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ የሚያደርግ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በዛሬው ዕለት የጀግናው አትሌት አበበ ቢቂላ መታሰቢያ ምስለ ቅርጽን በሮም አኑረዋል።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ ጉዳዩን አስመልከቶ በሰጡት ገለጻ ፣አበበ ቢቂላ በማይመች ሁኔታ ውስጥ በባዶ እግሩ የማራቶን ውድድርን በማሸነፍ ለመላ ጥቁር ህዝቦች የይቻላል መንፈስ ምልክት መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይ ጀግናው አትሌት ያስመዘገበው ድል በርካታ የአፍሪካ አገራት በቀኝ ግዛት ውስጥ እያሉ በመሆኑ ትርጉሙን ልዩ እንደሚያደርገው አስረድተዋል።

በመሆኑም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የአትሌቱን መታሰቢያ ምስለ ቅርጽ በሮም ለማቆም ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ስራ ሲያከናውኑ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

ለአብነትም ከሶስት ወራት በፊት ወደ ጣሊያን በመጡበት ወቅትም ይህንን ጉዳይ ትኩረት በመስጠት ከአገሪቷ ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎች ጋር መነጋገራቸውን አሰወታውሰው፣በዚህም በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤታማ ስራ ተከናውኗል ነው ያሉት።

መታሰቢያው ታሪክን ለትውልድ በመዘከር በኢትዮጵያ በየመስኩ የአገር ባለውለታ የሆኑ ጀግኖችን ለማፍራት መነሳሳትን ይፈጥራል ብለዋል።

በተጨማሪም በኢትዮጵያና በጣሊያን መካከል ያለውን ወዳጅነት ይበልጥ ለማጠናከር ሚናው የጎላ መሆኑንም ገልጸዋል።

የጀግናው አትሌት አበበ ቢቂላ መታሰቢያን በሮም ከተማ በማቆም ረገድ በጣሊያን የኢትዮጵያ ኤምባሲና የጣሊያን መንግስት ላከናወኑት ስራም በኢፌዴሪ መንግስት ስም ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም