ቀጥታ፡

በጋምቤላ ክልል ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎ ሊጠናከር ይገባል- ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ

ጋምቤላ ፤ሀምሌ 16/2015 (ኢዜአ)፦ በጋምቤላ ክልል ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን በሚደረገው ጥረት የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎ ሊጠናከር እንደሚገባ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ አስገነዘቡ።

ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በወቅታዊ የሰላምና ጸጥታ ጉዳዩች ዙሪያ ዛሬ ውይይት አካሂደዋል።

ርዕሰ መስተዳደሩ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት በክልሉ ሰሞኑን ተከስቶ የነበረውን የጸጥታ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት በሚደረገው ጥረት የተፎካካሪ ፓርቲዎች ተሳትፎ ሊጠናከር ይገባል።

ክልሉ ባለፉት አራት አመታት የተሻለ ሰላም የነበረበት ክልል እንደነበር አስታውሰዋል።

አሁን ላይ የተከሰተን የጸጥታ ችግር በመፍታት ሰላሙን ወደ ቀድሞ ለመመለስ በሚደረግ ጥረት በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ ርዕሰ መስተዳሩ አስገንዝበዋል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተንኳይ ጆክ በበኩላቸው ሰላም በሌለበት የፖለቲካም ሆነ የልማት ስራዎችን ለመከወን አስቻይ ሁኔታዎች እንደማይኖሩ ገልጸዋል።

ስለሆነም ለክልሉ ዘላቂ ሰላምና ልማት መረጋገጥ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።


 

የጋምቤላ ብሄራዊ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ተወካይ አቶ ኡቦንግ ኡሞድ በውይይቱ ላይ እንዳሉት ለተፈጠረው የጸጥታ ችግር የጋራ መፍትሄ ለመሻት ከክልሉ መንግስት ጋር በቅንጅት ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።  

"የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር በጋራ ለመፍታት መስራት ይገባል" ያሉት ደግሞ የጋምቤላ ህዝቦች ፍትህ ለሰላምና ልማት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄን በመወከል የተገኙት አቶ ሳይመን ቱት ናቸው።

የጋምቤላ ህዝቦች ነፃነት ንቅናቄ ተወካይ አቶ ኡማን ኦኬሎ በበኩላቸው ክልሉ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች በአንድነትና በአብሮት በሰላም የሚኖሩበት መሆኑን ተናግረዋል ።

"ይህንኑ መልካም የሰላም እሴት ለማስቀጠል ከሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚጠበቅ ጉዳይ ነው" ብለዋል።

በውይይቱ ላይ ብልጽግናን ጨምሮ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የአምስት  የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ተሳትፈዋል።    

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም