የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትና ትርፋማነቱን በሰራተኞቹ ጥረትና ትጋት በተጠናከረ መልኩ አስጠብቆ ይቀጥላል- የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትና ትርፋማነቱን በሰራተኞቹ ጥረትና ትጋት በተጠናከረ መልኩ አስጠብቆ ይቀጥላል- የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ
አዲስ አበባ ሀምሌ 16/2015(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትና ትርፋማነቱን በሰራተኞቹ ጥረትና ትጋት በተጠናከረ መልኩ አስጠብቆ የሚቀጥል መሆኑን የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ተናገሩ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ቀዳማዊ መሠረታዊ የሠራተኛ ማህበር 60ኛ ዓመት የአልማዝ እዮቤልዩ የተከበረ ሲሆን የማህበሩ አዲስ ሎጎ ተመርቋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ በመገኘት መልእክት ያስተላለፉት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው፤ አየር መንገዱ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪና ትርፋማ ሆኖ እንዲቀጥል በማድረግ ሂደት የሰራተኞች ሚና የላቀ መሆኑን ገልጸዋል።
የኮቪድ -19 ወረርሽኝ በዓለም አቀፍ ደረጃ አየር መንገዶችን የፈተነ እና ብዙ ጫና ያደረሰ መሆኑን አስታውሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተጽዕኖውን በመቋቋም በተወዳዳሪነትና ትርፋማነት መቀጠሉን ተናግረዋል።
ለዚህ ስኬት ደግሞ የአየር መንገዱ ሰራተኞች የላቀ ሚናቸውን በመወጣት የነበራቸውን ቁርጠኝነት አድንቀው ለሁሉም ሰራተኞችና ለአየር መንገዱ ተቀዳሚ መሰረታዊ የሰራተኞች ማኅበር ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
መሰረታዊ የሰራተኞች ማኅበሩ የኢንዱስትሪ ሰላምን ለማስጠበቅ፣ የሰራተኞችን መብትና ጥቅም ለማስከበር ከአየር መንገዱ የማኔጅመንት አባላት ጋር በቅርበትና በቅንጅት እየሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
በመሆኑም አየር መንገዱ የተመዘገቡ ስኬቶችን በማስቀጠል ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትና ትርፋማነቱን በተጠናከረ መልኩ በማስቀጠል የሰራተኞችን ውጤታማነት በመጨመር፣ የደንበኞችን አገልግሎትም ይበልጥ ለማሻሻል ይሰራል ብለዋል።
የአየር መንገዱ የሰራተኞችን መብትና ጥቅም የበለጠ ለማስጠበቅ እየሰራ መሆኑን የጠቀሱት ዋና ስራ አስፈፃሚው ቀደም ሲል ለ1 ሺህ 200 ሰራተኞች የመኖሪያ ቤት ገንብቶ ማስረከቡንም አስታውሰዋል።
በቀጣይም ለ5 ሺህ ሰራተኞች በ25 ቢሊየን ብር የመኖሪያ ቤት ለመገንባት ቦታውን ለኮንትራክተር አስረክበናል ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ቀዳማዊ መሠረታዊ የሠራተኛ ማህበር ፕሬዝዳንት ኪያ ለማ፤ ማኅበሩ የሰራተኞችን መብትና ጥቅም ለማስከበር፣ የኢንዱስትሪ ሰላምን ለማስከበር፣ ምቹ የሥራ ከባቢን ለመፍጠር እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
የሰራተኞችን ጥቅም ለማስጠበቅ ከባንኮች ጋር ትስስር በመፍጠር የቤትና የመኪና ብድር የሚያገኙበት እድል መመቻቸቱንም ጠቅሰዋል።
በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ክስተቶች ችግር ለገጠማቸው አካባቢዎችም ማህበሩ ድጋፍና እገዛ በማድረግም ማኅበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ስለመሆኑ አንስተዋል።
በማህበሩ አነሳሽነትና አስተባባሪነት በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ከአየር መንገዱ ሠራተኞች እና የማኔጅመንት አባላት የተሰበሰበ 2 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር ለክልሉ መንግስት ተወካይ መሰጠቱን ለአብነት ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ሰራተኞች ማህበራት ኮንፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ካሳሁን ፎሎ፤ በኢትዮጵያ የሰራተኛ ማህበራት ታሪክ ከ60 አመታት በፊት ህጋዊ እውቅና ካገኙ 29 ማህበራት ውስጥ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ቀዳማዊ መሰረታዊ የሰራተኛ ማኅበር 3ኛው እንደሆነ አስታውሰዋል።
አሁን ላይ ካሉት 2 ሺህ 300 ማህበራት መካከል የኢንዱስትሪ ሰላምን በማስጠበቅ እየሰሩ ካሉት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ቀዳማዊ መሰረታዊ የሰራተኞች ማኅበር በቀዳሚነት ይጠቀሳል ብለዋል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የሰራተኛ ማህበሩ አባላት ማህበሩ መብትና ጥቅማቸውን በማስጠበቅ በኩል ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ቀዳማዊ መሰረታዊ የሰራተኞች ማኅበር የተመሰረተበትን 60ኛ ዓመት ክብረ በዓል ላይ ለማህበሩ የስራ እንቅስቃሴ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት የእውቅና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።