በክልሎችና በከተማ አስተዳድሮች የመስክ ምልከታ ያደረገው የፌዴራል ከፍተኛ አመራሮች ቡድን በግኝቶቹ ላይ ተወያየ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሎችና በከተማ አስተዳድሮች የመስክ ምልከታ ያደረገው የፌዴራል ከፍተኛ አመራሮች ቡድን በግኝቶቹ ላይ ተወያየ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 15/2015(ኢዜአ)፦ በክልሎችና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ለ10 ቀናት የክትትልና ድጋፍ የመስክ ምልከታ ያደረገው የፌዴራል ከፍተኛ አመራሮች ቡድን በዋና ዋና ግኝቶቹ ላይ የጋራ ውይይት አካሄደ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በተካሄደው ውይይት ከተለያዩ ዘርፎች ተሰባጥሮ ከትግራይ ክልል በስተቀር በሁሉም የሀገሪቱ አቅጣጫ የተጓዘው የአመራር ቡድን በምልከታው ያሰባሰበውን መልካም ተሞክሮ እና ችግሮችን አቅርቧል።
ቡድኑ በዋናነት ምልከታውን ያካሄደው በሁሉም አካባቢዎች በክረምት በጎ ፈቃድ፣ በአረንጓዴ አሻራ፣ በሌማት ትሩፋት ፣ በመኸር ግብርና ፣ በገበታ ለትውልድ፣ በመንግሥት ገቢ አሰባሰብ፣ በኤክስፖርት አፈጻጸም ፣ በስራ እድል ፈጠራ እና የኑሮ ውድነት ቅነሳ ፣ በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ ፣ በአመራር አቅም ግንባታ እንዲሁም በጸጥታ ኃይል ሪፎርም ስራዎች ላይ ነው።
የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንትና የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ እንደገለጹት፣ የክትትልና ድጋፉ ዓላማ እያንዳንዱ ስራ ያለበትን ደረጃ በመለየት መልካም ተሞክሮዎች የሚሰፉበትን ጉድለቶች የሚሞሉበትን መንገድ መለየት ነው።
በተጨማሪም፣ በፌዴራል መንግስት እና በክልሎች እንዲሁም በከተማ አስተዳድሮች የበለጠ መቀናጀት እንዲፈጠር ማስቻል ነው ብለዋል።
ቡድኑ በምልከታው በሁሉም ዘርፍ በሀገር አቀፍ ደረጃ መልካም ጅምሮች መኖራቸውን አረጋግጧል።
ሆኖም ከዜጎች ፍላጎት እና ከሀገራዊ አቅም አንጻር አፈጻጸሙን በስፋት እና በጥራት ማሳደግ እንደሚገባም ማመላከቱን ከብልጽግና ፓርቲ ማህበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።