ቀጥታ፡

አካል ጉዳተኞች ዕድል ከተሰጣቸው ስኬታማ እንደሚሆኑ የኔ ልጅ ምስክር ናት - የተመራቂ ተማሪ ወላጅ አባት

አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 15/2015 (ኢዜአ) ፦ አካል ጉዳተኞች ዕድል ከተሰጣቸው ስኬታማ እንደሚሆኑ የኔ ልጅ ምስክር ናት ሲሉ አካል ጉዳተኛ ልጃቸውን ከኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያ ዲግሪ ያስመረቁ ወላጅ አባት ተናገሩ።

ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ መርሃ ግብሮች በዲፕሎማ፣ በመጀመሪያ ዲግሪና በሁለተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን 1 ሺህ 550 ተማሪዎችን ዛሬ አስመርቋል።

ዛሬ ለምርቃት ከበቁት መካከል ሰላማዊት ጎርፉ አንዷ ስትሆን በጂኦግራፊና አካባቢ ጥናት የመጀመሪያ ዲግሪዋን የያዘች አካል ጉዳተኛ ናት።

የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባት ተመራቂ ተማሪ ሰላማዊት የምትንቀሳቀሰውም በዊልቸር ነው።


 

እንዲያም ሆኖ ከኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ከ3 ነጥብ በላይ ውጤት በማስመዝገብ ለምርቃት የበቃች ሲሆን አካል ጉዳተኛ መሆን ማለት አለመቻል እንዳልሆነ በተግባር ማሳየት ችላለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትም ከተመራቂ ተማሪ ሰላማዊት አባት አቶ ጐርፉ አሰፋ ጋር ሰላማዊት ውጤታማ መሆን የቻለችበት ሚስጥሩ ምንድነው? ሲል ቃለ ምልልስ አድርጓል።

ለሰላማዊት ለውጤት መብቃት እንደ አባት እና እንደ ቤተሰብ የምንችለውን ሁሉ ድጋፍ አድርገናል ብለዋል።

አቶ ጎርፉ አሰፋ አክለውም የጎረቤትና የአካባቢው ሰው ድጋፍ ልጄን ለውጤት አብቅቷታል ይላሉ።

በዩኒቨርሲቲ ቆይታዋም በተለይም መምህራንና የዩኒቨርሲቲው አመራሮች ለልጄ የሰጡት ድጋፍ በጣም የሚያስደስት ነው፤ ለተገኘው ውጤትም አዎንታዊ አስተዋጽኦ አበርክቷል ሲሉም ነው ያብራሩት።

አካል ጉዳተኞች ዕድል ከተሰጣቸው ስኬታማ እንደሚሆኑ የኔ ልጅ ምስክር ናት ያሉት አቶ ጎርፉ አካል ጉዳተኞችን ማሳተፍና የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል።

አካል ጉዳተኞች ማድረግ ይችላሉ፣ መማር ይችላሉ፤ ለስኬት መብቃትም ይችላሉ የሚለው እሳቤ አሁንም ማኅበረሰቡ ውስጥ በሚጠበቀው ደረጃ እንዳልጎለበተ የሚጠቅሱት አቶ ጎርፉ በዚህ ላይ ኅብረተሰቡ መሰረታዊ የሆነ የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት እንደሚኖርበት አጽንኦት ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም