እናቴ ከእናትነት ድርሻዋ በላይ የአባቴን ሚና ደርባ ተስፋዬን አለምልማልኛለች -የማዕረግ ተመራቂው እሸቱ ወላቦ - ኢዜአ አማርኛ
እናቴ ከእናትነት ድርሻዋ በላይ የአባቴን ሚና ደርባ ተስፋዬን አለምልማልኛለች -የማዕረግ ተመራቂው እሸቱ ወላቦ
ጂንካ ፤ ሐምሌ 15/2015(ኢዜአ)፦ ''እናቴ ከእናትነት ድርሻዋ በላይ የአባቴን ሚና ደርባ ተስፋዬን አለምልማልኛለች '' ይላል እጅግ በላቀ ውጤት ትምህርቱን ያጠናቀቀው የጅንካ ዩኒቨርሲቲ የዘንድሮ የማዕረግ ተመራቂ እሸቱ ወላቦ።
በትምህርት ዘመኑ ላለፈባቸው ውጣ ውረዶችና ለደረሰበት ውጤት የእናቱን ድርብ አስተዋጽኦ ወሳኝ እንደነበረ ይናገራል።
በዩኒቨርሲቲ ቆይታውም ከወሰዳቸው ከ56 ኮርሶች 48ቱን በ'ኤ ፕላስ' ፤ቀሪዎቹን ደግሞ 'ኤ' በማምጣት የዩኒቨርሲቲው ባለ እጅግ ከፍተኛ ማዕረግ ተመራቂ ሆኗል።
በኦሮሚያ ክልል በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ቀርሳ ማሌማ ወረዳ የተወልደው እሸቱ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በጌቶ ኢላላ ዋቆ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትሏል።የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በሌመን ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት ተከታትሎ በ2011 ዓ.ም አጠናቋል።
እሸቱ እንዳለው ለዚህ ውጤት የበቃው መንገዶች ሁሉ አልጋ ባልጋ ሆኖለት ሳይሆን ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፎ ነው።
በትምህርቱ እንዲጎብዝ ሲያጠና ከጎኑ ሆነው ያበረታቱት የነበሩትን አባቱን የስምንተኛ ክፍል ሞዴል ፈተና ሲፈተን በሞት መነጠቁን ተናግራል።
በእሳቸው ሞት ምከንያት ተስፋ ቆርጦ ትምህርቱን ለማቋረጥ ወስኖ እንደነበር ገልጾ፣ በወቅቱ ኅዘኑን ዋጥ አድርጎ ሞዴል ፈተናውን ተፈትኖ ማጠናቀቁን እና እናቱን ላለማስከፋት ትምህርቴን ጠንክሮ መማር መቀጠሉን አስረድቷል።
የማረዕግ ተመራቂው እሸቱ እንዳለው የአባቱ ሀዘን ስለበረታበት ስምንተኛ ክፍል ጥሩ ውጤት ማምጣት አልቻለም፤ ዘጠነኛ ክፍል ሲገባ ግን ጠንክሮ መማር እንዳለበት ራሱን አሳመነ።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በሌመን ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ተከታትሎ በ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና የተሻለ ውጤት አምጥቶ በ2012 ጂንካ ዩኒቨርሲቲን መቀላቀሉን ይናገራል።
ጂንካ ካለበት አካባቢ በጣም ሩቅ በመሆኑ በዩኒቨርሲቲው ሲመደብ ''ልሂድ አልሂድ'' በሚል ሃሳብ ከራሱ ጋር ሙግት ገጥሞ ነበር አስታውሶ፤ ወደ ጂንካ ሲመጣ ግን ከቦታው ርቀት በላይ የሕዝቡ ፍቅር እንደገዛው ገልጿል።
እሸቱ አክሎም 'እናቴ ከእናትነት ድርሻዋ ባሻገር የአባቴን ሚና ደርባ ተስፋዬን አለምልማልኛለች '' ሲል በትምህርቱ ውጤታማ እንዲሆን የእናቱ ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን ገልጿል።
''ግብርና የአገሪቱ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት እንደመሆኑ በእውቀትና በቴክኖሎጂዎች መታገዝና ምርታማነቱን ማሳደግ እንደሚገባ አምናለሁ፤ አገሬ የኔን ዕውቀት እንደምትሻ ጠንቅቄ እረዳለሁ'' ይላል የከፍተኛ ማዕረግ ተመራቂው እሸቱ ወላቦ።
ከልጅነቱ ጀምሮ ግብርናን በሳይንሳዊ መንገድ የማጥናትና ለአርሶ አደሩ ችግር ፈቺ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን የማመንጨት ህልም እንደነበረው ገልጾ፤ በዩኒቨርሲቲው አግሮ ኢኮኖሚክስ የትምህርት ክፍል ሲመደብ "ደስታዬ ወደር አልነበረውም" ብሏል።
የተመደበበት የትምሀርት ዘርፍ መማር የሚፈልገውና የሚወደው በመሆኑ ጠንክሮ እንዲማርና ለላቀ ውጤት እንዲበቃ እንዳደረገው ተናግሯል።
አብዛኛዎቹ ተማሪዎች ከማጥናት ይልቅ የሽምደዳ ንባብ ላይ እንደሚያተኩሩና የሽምደዳ ንባብ ፈተና ከማለፍ በዘለለ ዘላቂ ዕውቀት አያስገኝም የሚለው እሸቱ፤ ከሽምደዳ ንብባ ይልቅ ነገሮችን በጥልቀትና በስፋት ተንትኖ በረዳት ማጥናት ውጤታማ ያደርጋል ብሏል።
በዩኒቨርሲቲው የምረቃ ሥነሥርዓት ''የዋንጫ፣የወርቅ ሜዳልያ እና የላፕቶፕ ተሸላሚ መሆኔ ልገልፀው የማይችለው ደስታ ተሰምቶኛል፤ፈተናዎችን ተቋሜ ጠንክሬ መስራቴ ለስኬት አብቅቶኛል'' ብሏል።
በዩኒቨርሲቲው ቆይታው በቀሰመው ዕውቀት በግብርናው ዘርፍ የተለያዩ ጥናቶችን በማካሄድ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የማፍለቅ የአርሶ አደር ኑሮ የማሻሻል ዕቅድ እንዳለውም ተናግሯል።
እናም ''በተቻለኝ አቅም ግብርናውን በሳይንሳዊ ምርምርና በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ማሳደግ ላይ በሙሉ አቅሜ መስራት እፈልጋለሁ'' ሲል የወደፊት ህልሙን ገልጿል።
የማዕረግ ተመራቂው እሸቱ ታላቅ እህት ወይዘሮ ባህርነሽ ወላቦ ''እሸቱ ለዚህ ደረጃ እንደሚደርስ ጠንቅቄ አውቅ ነበር'' ይላሉ።
''ከልጅነቱ ጀምሮ ለትምህርት ያለው ፍቅር ልዩ ነው፤ በአንድ ማዕድ ቀርበን እየበላ እንኳ በአንድ እጁ ደብተሩን ይዞ ያጠና ነበር'' ሲሉም ትውስታቸውን አጋርተዋል።
እሸቱ በዕውቀት ብቻ ሳይሆን በባህርዩም ምስጉን ነው የሚሉት እህቱ ፣ሰው አክባሪና ተግባቢ መሆኑ ከጥረቱ ባሻገር ለስኬቱ አስተዋጽኦ አድርጎለታል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።
''በቀጣይም ወንድሜ በቀሰመው ዕውቀት በሙሉ አቅሙ አገሩን እንዲያገለግል እመኛለሁ'' ሲሉም አዲስ በሚጀምረው ሕይወት መልካም ምኞታቸውን ወይዘሮ ባህርነሽ ገልጸዋል።
ከትምህርት ክፍሉ 3 ነጥብ 85 በማምጣት በማዕረግ የተመረቀው የእሸቱ የልብ ጓደኛ አሼ ገልቾ ስለእሸቱ ብርቱነት እማኝነቱን የሰጠው እንደህ ሲል ነው።
እሸቱ ከራሱ አልፎ ለሌሎችም የሚያስብ በውጤት ዝቅ ያሉ ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዲያመጡ የሚጥር ቀናዒ ሰው ነው ሲል የልብ ጓደኛውን ገልጾታል።
''ለእኔ የተሻለ ውጤት ማምጣት የእርሱ እጅ አለበት'' የሚለው ተማሪ አሼ፤''ስደክም እያገዘኝ ወደኋላ ስቀር እያበረታታኝ ይህን ውጤት እንዳስመዘግብ ረድቶኛል ብሏል።
አሼ እክሎም "ለዚህም ጥልቅ ፍቅርና ላቅ ያለ ምስጋና አለኝ'' ለከፍተኛ የማዕረግ ተመራቂው የልብ ጓደኛውን፤ የወደፊቱን የኢትዮጵያ ግብርና ባለራዕይውን አሞካሽቶታል።
እሸቱ ፍሬ ሊሆን ተዘጋጅቷል፤ባለፉት ዓመታት ፍሬያማ እየሆነ የመጣውን የግብርናው ዘርፍ በይበልጥ ፍሬያማ ለማድረግ በሰለጠንበት ሙያ ሰርቶ ምርትና ምርታማነት ሊያሳድግ ፅኑ አቋሙን ገልጿል።
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያስተማራቸውን ከ500 በላይ ተማሪዎችን ከትናንት በስትያ ማስመረቁ ይታወሳል።